የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 16

16
የነቢዩ ኤርምያስ አለማግባቱና መልእክቱ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ። 3ጌታ በዚህ ስፍራ በተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ በወለዱአቸውም እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር በወለዱአቸው አባቶቻቸው ላይ እንዲህ ይላልና፦ 4በክፉ በሽታ ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።
5“ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰላሜን፥ ቸርነትንና ጽኑ ፍቅርን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ለማልቀስም ሆነ ለማዘን አትሂድ። 6ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም፥ ሰዎችም አያለቅሱላቸውም፥ ስለ እነርሱም ማንም ገላውን አይነጭም ራሱንም አይላጭም፤ 7ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የኀዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። 8ለመብላትና ለመጠጣት፥ ከእነርሱም ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ። 9#ኤር. 7፥34፤ 25፥10፤ ራእ. 18፥23።የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም፥ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራቱይን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።
10“ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃላት ሁሉ በተናገርህ ጊዜ፦ ‘ይህን ሁሉ ታላቅ የሆነ ክፉ ነገርን ለምን ጌታ ተናገረብን? በደላችንስ ምንድነው? በአምላካችንስ በጌታ ላይ የሠራነው ኃጢአታችን ምንድነው?’ ቢሉህ፥ 11አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተው ነው፥ ይላል ጌታ፥ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አገለገሉአቸውም ሰገዱላቸውም፥ እነርሱም ትተውኛል፥ ሕጌንም አልጠበቁም፤ 12እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም፥ ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ እልከኝነት ሄዳችኋል እኔንም አልሰማችሁም። 13ስለዚህ ከዚህች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወዳላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።’
ጌታ ሕዝብን ከምርኮ ይመልሳል
14“ስለዚህ፥ እነሆ፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ተብሎ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ 15ነገር ግን፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
16“እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ፥ ይላል ጌታ፥ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እልካለሁ፥ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድኑአቸዋል። 17ዓይኔ በመንገዶቻቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ከፊቴም አልተሰወሩም፥ ኃጢአታቸውም ከዓይኔ አልተሸሸገም። 18ምድሬንም በተጠሉ ጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኃጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።”
19አቤቱ! ኃይሌ፥ አምባዬ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ፥ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፦ “በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር የማይረባቸውንም ወርሰዋል፤ 20በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክት አድርጎ ይሠራልን?”
21“ስለዚህ፥ እነሆ፥ አስታውቃቸዋለሁ፥ በዚህች ጊዜ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ ጌታ እንደሆነ ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ