ትንቢተ ኤርምያስ 14
14
ታላቁ ድርቅ
1ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። 2“ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ ስለ ምድሪቱም አለቀሱ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሏል። 3ታላላቆቻቸውም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ላኩ፤ ወደ ጉድጓድ መጡ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፤ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ። 4በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለሆነ አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ። 5ዋላ ደግሞ በምድረ በዳ ወለደች፥ ሣርም የለምና ግልገልዋን ተወች። 6የሜዳ አህዮችም በተራቈቱ ኮረብቶች ላይ ቆመዋል፥ እንደ ቀበሮም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ልምላሜም የለምና ዐይኖቻቸው ጠወለጉ።
7“ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአትን ሠርተናል፤ ምንም እንኳ ኃጢአታችን ቢመሰክርብንም ስለ ስምህ ብለህ አቤቱ! አድርግ። 8አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ! በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድሪቱ እንደ እንግዳ፥ ሌሊቱን ለማሳለፍ ወደ ማደርያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ለምን ትሆናለህ? 9ግራ እንደ ተጋባ ሰው፥ ለማዳንም እንደማይችል ኃያል ለምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ! በመካከላችን ነህ፥ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን።”
10ጌታ ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “በእውነት መቅበዝበዝን ወድደዋል፥ እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ ጌታ በእነርሱ ደስ አይሰኝም፥ በደላቸውንም አሁን ያስታውሳል ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።” 11ጌታም፦ “ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው። 12በጾሙ ጊዜ ልመናቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ ይልቁንም በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ” አለኝ።
ሐሰተኛ ነብያትን ማውገዝ
13እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! እነሆ፥ ነቢያት፦ ‘ዘላቂ ሰላም በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፥ ራብም አያገኛችሁም’ ይሉአቸዋል” አልሁ። 14ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ነቢያቱ በስሜ የውሸትን ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸትን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል። 15ስለዚህ ጌታ በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት፦ ‘በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም’ ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል፦ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ። 16ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይጣላሉ፤እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም፤ ክፋታቸውንም በእነርሱ ላይ አወርድባቸዋለሁ። 17ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና ፈጽሞ በማይሽር ቁስል ቆስላለችና ዐይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፍስሱ። 18ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ፥ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ፥ በራብ ደዌ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቁት አገር ሄደዋልና።’”
ከጌታ ሕዝቡ ምሕረትን መለመኑ
19በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለምን መታኸን? ፈውስስ ስለምን የለንም? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። 20አቤቱ! በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን። 21ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፥ የክብርህንም ዙፋን አታዋርድ፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስታውስ እንጂ አታፍርስ። 22በውኑ በአሕዛብ ከንቱ ጣዖታት መካከል ዝናብን ሊያዘንብ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ካፊያን መስጠት ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ! አንተ አይደለህምን? አንተ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ