የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የያዕቆብ መልእክት 1:2-15

የያዕቆብ መልእክት 1:2-15 መቅካእኤ

ወንድሞቼ ሆይ! ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ደስታ አድርጋችሁ ቁጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን እንደሚያጸናችሁ ታውቃላችሁ፥ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን እንድትሆኑ ጽናትም ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚነዋወጥ የባሕርን ማዕበል ነው። ያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች አገኛለሁ ብሎ ሊያስብ አይገባውም። በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ሁለት ሐሳብ ያለው ሰው ነው። ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ፥ ሀብታምም እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በውርደቱ ይመካ። የፀሐይ ቃጠሎ በንዳዱ ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የመልኩም ውበት ይጠፋል፤ እንዲሁ ሀብታም ሰው በመንገዱ ይዝላል። ጌታ ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ተፈትኖ ይቀበላልና፥ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።