ትንቢተ ኢሳይያስ 66:19-24

ትንቢተ ኢሳይያስ 66:19-24 መቅካእኤ

በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ያዋን፥ በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ። የእስራኤል ልጆች ቁርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ ጌታ ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁም ለጌታ ቁርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል ጌታ። ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል ጌታ። እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል ጌታ። እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ለመስገድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል ጌታ። ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።