የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 48

48
1እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ ከይሁዳም ውኆች የወጣችሁ፥ በጌታ ስም የምትምሉ፥ በእውነት ሳይሆን በጽድቅም ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ፥ 2በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ። 3የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፥ ከአፌም ወጥቶአል፥ አሳይቼውማለሁ፤ ድንገት አድርጌው ተፈጽሞዋል። 4አንተ እልከኛ፥ አንገትህን የብረት ጅማት፥ ግንባርህም ናስ እንደሆነ አውቄአለሁ፤ 5ስለዚህ፥ አንተ፦ “ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፥ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌ ይህን አዘዙኝ” እንዳትል፥ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር፥ ከመሆኑም በፊት አሳይቼህ ነበር። 6ሰምተሃል፤ አሁን ይህን ሁሉ ተመልከት፤ ይሄን ራስህ አትመሰክርም? የተሰወሩትን ያላወቅሃቸውንም አዲስ ነገሮችን ከአሁን ጀምሬ አሳይችኋለሁ። 7እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፤ አንተም፦ “እነሆ፥ አስቀድሜ አውቄአቸዋለሁ” እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም። 8አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ጆሮህ ከጥንት አልተከፈተችም፤ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደሆንህ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደ ተጠራህ አውቄአለሁና። 9ስለ ስሜ ቁጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳለጠፋህም ስለ ምስጋናዬ እታገሣለሁ። 10እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ። 11ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ፤ ስለምን ስሜ ይነቀፋል? ክብሬን ለሌላ አልሰጥም። 12#ኢሳ. 44፥6፤ ራእ. 1፥17፤ 22፥13።ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። 13እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። 14እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? ጌታ የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። 15እኔ እራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። 16ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርኩም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርኩ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።
17ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ ጌታ ነኝ። 18ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤ 19ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፥ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። 20#ራእ. 18፥4።ከባቢሎን ውጡ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፥ ይህንንም ንገሩ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩ፦ “ጌታ ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል!” በሉ። 21በምድረ በዳ በኩል በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፤ ውኃንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፥ ዓለቱንም ሰነጠቀ ውኃውም ፈሰሰ። 22#ኢሳ. 57፥21።“ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል ጌታ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ