የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 37

37
የሕዝቅያስ ኢሳይያስን ማማከር
1ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ ጌታም ቤት ገባ። 2የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። 3እነርሱም፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ብርታቱ የለም። 4ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ አለቃው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ ጌታ ሰምቶ እንደሆነ፥ አምላክህ ጌታም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደሆን፥ ስለዚህ አንተም በሕይወት ስለተረፉት ቅሬታ ጸልይ አሉት።” 5ከዚያም የንጉሡ የሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ መጡ። 6ኢሳይያስም፥ “ለአለቃችሁ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም ላይ በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት’ ” አላቸው። 8ራፋስቂስም ተመለሰ፤ የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ስለ ነበር በልብና ከተማ ሲዋጋ አገኘው። 9የአሦርም ንጉሥ፦ “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቷል” የሚል ወሬ ሰማ። ይህን በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ እንዲህም አለው፦ 10“ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክ አያታልህ። 11እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? 12አባቶቼ ያጠፉአቸውን ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፍስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸው? 13የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?”
14ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ጌታ ቤት ሕዝቅያስም ወጥቶ በጌታ ፊት ዘረጋው። 15ወደ ጌታ እንዲህ በማለት ሕዝቅያስ ጸለየ፦ 16#ዘፀ. 25፥22።“አቤቱ የሠራዊት ጌታ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። 17ጌታ ሆይ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ለመገዳደር የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። 18ጌታ ሆይ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፤ 19አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ፥ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 20እንግዲህም አምላካችን ጌታ ሆይ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ ጌታ እንደሆንህ እንዲያውቁ ከእጁ አድነን።”
21የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ለምነሀልና 22ጌታ ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ስትሸሽ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። 23የተገዳደርኸው የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደርግህበት፥ ዓይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ አይደለምን!’ 24አንተም እንዲህ አለክ፦ በሠረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሲባኖስ ጥግ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹን ዝግባዎች፥ የተመረጡትን ጥንዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ፤ 25ቈፈርኩ ውኃም ጠጣሁ፥ የግብጽንም ወንዞች ሁሉ በእግሬ ጫማ አደረቅኩ።” 26ይህን እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? እሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግኩ። 27ስለዚህ የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሏል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለመለመም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል። 28እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቁጣ አውቄአለሁ። 29ቁጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ።
30ይህ ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዳላችሁ፤ ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ። 31የተረፈው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል። 32ከኢየሩሳሌም ቅሬታ፥ ከጽዮን ተራራ ያመለጡት ይመጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ ቅንዓት ይህን ያደርጋል። 33“ስለዚህም ጌታ ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም አይደለድልባትም። 34በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፤ ወደዚችም ከተማ አይመጣም፥ ይላል ጌታ። 35ስለ እኔም ስለ አገልጋዬም ዳዊት ይህችን ከተማ አድናታለሁ፥ እጋርዳታለሁም።”
የሰናክሬም ሽንፈትና ሞት
36የጌታም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። 37የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 38በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ