ትንቢተ ኢሳይያስ 16
16
1በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ በምድር ላይ ገዢ ለሆነው ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ የበግ ጠቦቶችን ስደዱ። 2ከጎጆቸው ተበትነው እንደሚበሩ ወፎች፥ የሞዓብ ሴቶችም በአርኖን መሻገሪያዎች እንዲሁ ይሆናሉ። 3ምክርን ለግሺ፥ ፍትህን አስፍኚ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አጢይ፤ ስደተኞችን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አሳልፈሽ አትስጪ። 4ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ዘንድ ይኑሩ፤ ስደተኞቹን ከሚሳድዷቸው መሸሸጊ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቷል፤ ጨቋኞች የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። 5ዙፋኑም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም በዳዊት ድንኳን ፍትህን የሚሻ ትክክል የሆነውን ለመፈጸም የሚፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል። 6የሞዓብን ኩራት፥ እጅግ መታበዩን! ስለ እብሪቱና ስለ ኩራቱ፥ ስለ ስድነቱም ሰምተናል፤ ትምክሕቱ ከንቱ ነው። 7ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማ፤ ሁሉም ዋይታ ያሰማሉ፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። 8የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች ኢያዜርን አልፈው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቁጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። 9ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ግንድ ከኢያዜር ልቅሶ ጋር አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አርስሻለሁ። 10ደስታና ሐሴትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፤ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። 11ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ በገና የኀዘን እንጉርጉሮ ታሰማለች። 12ሞዓም ወደ ኮረብታ ወጥቶ ራሱን ቢያደክም፥ ለጸሎት ወደ መቅደሱ ቢገባም በከንቱ ይደክማል እንጂ አያሸንፍም። 13ጌታ በሞዓብ ላይ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ይህ ነው። 14አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ተቀጣሪ ደሞዝተኛ የሞዓብ ክብር፥ ምንም ያህል ሕዝቡ ቢበዛ፥ በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚተርፈውም ሕዝብ እጅግ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 16: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ