ትንቢተ ኢሳይያስ 10
10
1ፍትሕ የጐደለውን ሕግ ለሚያወጡ፤ ጭቈና የሞላበትን ሥርዓት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! 2የድኾችን መብት ለሚገፉ፤ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፤ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፤ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው! 3በምትጎበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል? ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ? ርዳታን ለማግኘትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ሀብታችሁንስ የት ታገኙታላችሁ? 4ከእስረኞች ጋር ከመርበትበት፤ ከታረዱትም ጋር ከመጣል በቀር ምንም አይተርፋችሁም። ይህም ሁሉ ሆኖ፤ ቁጣው ገና አልበረደም። እጁም እንደ ተዘረጋ ነው።
የእግዚአብሔር ፍርድ በአሦር ላይ
5 #
ኢሳ. 14፥24-27፤ ናሆም 1፥1—3፥19፤ ሶፎ. 2፥13-15። የቁጣዬ በትር ለሆነ፤ የመቅሠፍቴም ዱላ በእጁ ላለው ለአሦራዊው ወዮለት! 6ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፤ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፤ እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፤ አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፤ በሚያስቆጣኝም ሕዝብ ላይ እሰደዋለሁ። 7እርሱ ግን እንዲህ አላሰበም፤ በልቡም ይህ አልነበረም፤ ነገር ግን ዕቅዱ ለማጥፋት፤ ብዙ ሕዝቦችንም ለመደምሰስ ነበር። 8እንዲህም ይል ነበር፤ “የጦር አዛዦቹ በሙሉ ነገሥታት አይደሉምን? 9ካልኖ እንደ ከርከሚሽ፤ ሐማት እንደ አርፋድ፤ ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደሉምን? 10የጣዖታትን መንግሥታት፤ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ መንግሥታት የሚበልጡትን እጄ እንደ ያዘች ሁሉ፤ 11በሰማርያና በጣዖቶቿ ያደረግሁትን፤ በኢየሩሳሌምና በተቀረጹ ምስሎቿስ እንዲሁ አላደርግምን?” 12ጌታ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ የሚያደርገውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፤ እንዲህ ይላል የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ፤ 13የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፤ “‘ይህን ሁሉ ያደረግሁት በክንዴ ብርታት ነው፤ ደግሞም በጥበቤ አስተዋይ ነኝና። የመንግሥታትን ድንበር አፈረስሁ፤ ሀብታቸውን ዘረፍሁ፤ ነገሥታታቸውን እንደ አንድ ኀያል ሆኜ አዋረድሁ። 14ሰው እጁን ወደ ወፍ ጎጆ እንደሚሰድ፤ እኔም እንዲሁ እጄን ወደ መንግሥታት ሀብት ሰደድሁ፤ ሰዎች የተተወ ዕንቁላል እንደሚሰበስቡ፤ እኔም እንዲሁ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ ክንፉን ያራገበ የለም፤ አፉንም ከፍቶ የጮኸ አልነበረም።’” 15መጥረቢያ በሚቆርጥበት ሰው ላይ ይኩራራልን? መጋዝስ በሚስበው ላይ ይታበያልን? በትር በሚያነሣው ሰው ላይ ራሱን እንደሚነቀንቅ፤ ዘንግም ዕንጨት እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚኩራራ ነው። 16ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤ ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት ይለኰሳል። 17የእስራኤል ብርሃን እሳት፤ ቅዱሱም ነበልባል ይሆናል፤ በአንድ ቀንም እሾኹንና ኩርንችቱን እሳት ይበላዋል፤ 18ሕመምተኛ እየመነመነ እንደሚሞት፤ የደኑን ክብርና የለማውን ዕርሻ፤ ነፍስና ሥጋንም ፈጽሞ ያጠፋል። 19በደኑ ውስጥ የሚተርፉት ዛፎች በጣም ጥቂት ናቸው፤ ሕፃን ልጅ እንኳ ቆጥሮ ሊመዘግባቸው ይችላል።
የተረፉት የእስራኤል ዘሮች
20በዚያን ቀን ከእስራኤል ዘር የተረፉት፤ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመታቸው ላይ አይታመኑም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በጌታ ላይ፤ በእውነት ይታመናሉ። 21የተረፉት ይመለሳሉ፤ ከያዕቆብ ቤት የተረፉት እንኳን ሳይቀሩ ወደ ኀያሉ አምላክ ይመለሳሉ። 22#ሮሜ 9፥27።እስራኤል ሆይ፤ ሕዝብህ እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም፤ የተረፉት ብቻ ይመለሳሉ። ታላቅና ጻድቅ የሆነ ጥፋት ታውጆአል። 23ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ የወሰነውን ጥፋት በምድር ሁሉ ላይ ያመጣል። 24ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በጽዮን የምትኖሩ ሕዝቤ ሆይ፤ ግብጽ እንዳደረገብህ ሁሉ በትር ያነሡብህን፤ በሽመል የደበደቡህን አሦራውያንን አትፍራቸው። 25በአንተ ላይ ያመጣሁትን ቅጣት በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቆማለሁ፤ በእነርሱም ላይ መዓቴን አመጣለሁ።” 26የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድያምን በሔሬብ ዐለት አካባቢ እንደ መታ፤ በጅራፍ ይገርፋቸዋል፤ በግብጽ እንዳደረገውም ሁሉ፤ በትሩን በውሆች ላይ ያነሣል። 27በዚያን ቀን ሸክማቸው ከትከሻህ፤ ቀንበራቸውም ከዐንገትህ ላይ ይነሣል፤ ከውፍረትህም የተነሣ ቀንበሩ ይሰበራል። 28ወደ ዐያት ይገባሉ፤ በሚግሮን ያልፋሉ፤ ጓዛቸውንም በማክማስ ያከማቻሉ። 29መተላለፊያውን ዐልፈው እንዲህ ይላሉ፤ “በጌባዕ ሰፍረን እናድራለን።” ራማ ደነገጠች፤ የሳኦል ከተማ ጊብዓ ሸሸች። 30የጋሊም ሴት ልጅ ሆይ፤ ጩኺ! ላይሻ ሆይ፤ አድምጪ! ምስኪን ዓናቶት ሆይ፤ መልሺላት! 31ማድሜናህ በሽሽት ላይ ነች፤ የጌቢም ሕዝብ ሊደበቅ ይሮጣል። 32በዚህ ቀን ኖብ ይደርሳሉ፤ እጃቸውን በኢየሩሳሌም ኰረብታ፤ በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ላይ በዛቻ ነቀነቁ። 33እነሆ፥ ልዑል እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ፤ በታላቅ ኃይል ቅርንጫፎችን ይቈራርጣል፤ ረጃጅም ዛፎች ይገነደሳሉ፤ ከፍ ከፍ ያሉትም ይወድቃሉ። 34ጥቅጥቅ ያለውን ደን በመጥረቢያ ይቈራርጣል፤ ሊባኖስም በኀያሉ ፊት ይወድቃል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ