የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ

መግቢያ
ትንቢተ ሆሴዕ ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት መካከል የመጀመርያው ነው። የብኤሪ ልጅ ነቢዩ ሆሴዕ የተወለደውና ትንቢቱን የተናገረው በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ነው። በመጽሐፉ የመጀመርያዎቹ ምዕራፎች እግዚአብሔር ሆሴዕን በመጥራት አመንዝራይቱን ጎሜርን እንዲያገባ ያዘዋል፤ እርስዋም ኢይዝራኤልና ሎዓሚ የሚባሉ ሁለት ወንድ ልጆችንና ሎሩሃማ የምትባል አንዲት ሴት ልጅ ትወልድለታለች። ነቢዩ ሆሴዕ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያለውን የቃል ኪዳን ትስስር ለማሳየት ጋብቻንና (ባልንና አመንዝራይቱ ሚስትን) (1-3) ቤተሰብን (ወላጅንና ዓመፀኛ ልጅን) (11፥1-7) እንደ ምሳሌ ተጠቅሞአል። ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል የጋብቻን ምሳሌ በመጠቀም የመጀመርያው ነው። ሚስት (እስራኤል) ታማኝነትዋን በማጕደል ወደ ሌሎች አፍቃሪዎችዋ ስትሄድ ታማኝ አፍቃሪ በሆነው ባልዋ (እግዚአብሔር) ላይ የምታደርስበትን ጽኑ መከራና ውስጣዊ የስሜት ሥቃይ በተምሳሌታዊ መንገድ ይገልጻል። እንዲሁም እምነት ያጎደለችው ሚስት ወደ ልቦናዋ እንድትመለስና እንድትማር ታማኝ አፍቃሪ ባልዋ በቊጣ ይናገራታል፤ ይቀጣታልም (4፥10፤ 9፥2፤ 7፥16፤ 8፥13፤ 11፥5)። የእስራኤል ሕዝብ የሚተላለፉበትን በቤቴልና በጌልገላ የሚገኙትን የጣዖት የማምለክያ ስፍራዎችን ያወግዛል (4፥15 9፥15)። እስራኤል እምነት በማጕደልዋ፤ ታማኝ ባለመሆንዋና ጌታዋን ባለማወቅዋ ባጠቃላይ የቃል ኪዳኑን ሕግ በማፍረስዋ እግዚአብሔር እርስዋን መክሰሱን ይናገራል (4፥1 5፥1)። ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት በሆሴዕ በምዕራፍ ሁለት ላይ በማራኪ የፍቅር ቃል ተገልጿል። ስለዚህ እስራኤል በሠራዊትዋ ኃያልነት ላይ በመመካት ከሌሎችም የውጭ ኃይሎች (ከአሦርና ከግብጽ) ጋር ቃል ኪዳን በማድረግና በዓልን በማምለክ ከጌታ ጋር የነበራትን ቃል ኪዳን ማፍረስዋን ነቢዩ ይገልጻል። በመጨረሻም እምነት ያጎደለችው ሚስት ወደ ባልዋ፥ ዓመፀኛው ልጅም ወደ ወላጆቹ፥ በንስሐ ለመመለስ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ጉዞ ያወሳል። ስለሆነም እስራኤል ንስሐ ገብታ (10፥12) ለእግዚአብሔር ብትታመንና የቃል ኪዳኑን ሕግ ብትጠብቅ (12፥7) እርሱ ቊስሏን እንደሚፈውስ፥ ስብራትዋንም እንደሚጠግን፥ በሕይወትም እንደሚያኖራት (6፥1-2)፥ ፍሬያማ እንደሚያደርጋት፥ ከስደት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚመልሳትና (6፥11፤ 11፥10-11) በእርሱም ጥላ ሥር እንደሚያኖራት (14፥8) ይናገራል።
የትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ በምዕራፍ አንድ ቊጥር አንድ ላይ ይገኛል። ከዚያም በምዕራፍ ዐሥራ አራት ቊጥር ዐሥር ላይ በቀረበው የመደምደምያ ሐሳብ ይፈጸማል። መጽሐፉም በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው ክፍል ከምዕራፍ አንድ ቊጥር ሁለት እስከ ምዕራፍ ሦስት ቊጥር አምስት ያለው ሲሆን ነቢዩ ስለ ፈጸመው ጋብቻና ይህም ስለሚያመለክተው ምሳሌ ይናገራል። ሁለተኛው ክፍል ከምዕራፍ አራት ቊጥር አንድ እስከ ምዕራፍ ዐሥራ አራት ቊጥር ዐሥር ያለው ሲሆን ስለ እስራኤል በደል፤ ቅጣትና መታደስ ይገልጻል።
የትንቢተ ሆሴዕ መልእክት በዋነኛነት ፍቅርን፤ እግዚአብሔርን ማወቅን፤ ታማኝነትንና ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መመለስን የሚመለከት ነው። እስራኤል የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን መጠበቅ እንዲችል እግዚአብሔርን ማወቅና ከኃጢአቱ በንስሐ ተመልሶ በፍቅር ለእርሱ ታማኝ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል። እግዚአብሔር የሚሻው፦ “ከመሥዋዕት ይልቅ ጽኑ ፍቅርን፥ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ” (6፥6) ነውና።
ምዕራፍ

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ