የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 6:1-22

ኦሪት ዘፍጥረት 6:1-22 መቅካእኤ

የሰው ዘር በምድር ላይ እየበዛ በሄደ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱ፥ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፥ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። ጌታም፦ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፥ እድሜውም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናል” አለ። በዚያን ዘመን ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፥ እና ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፥ እነርሱም በዱሮ ዘመን፥ ስማቸው የታወቀ፥ ኃያላን ሆኑ። ጌታም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩም ጌታ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። በዚህ ምክንያት ጌታ፥ “ከምድር ላይ የፈጠርኩትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ሰው እና አራዊትን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን እና የሰማይ አእዋፍንም፥ ስለ ፈጠርኳቸው ተጸጽቼአለሁና” አለ። ይሁን እንጂ ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንደሚከተለው ነው። ኖኅም ጻድቅ፥ በትውልዱም በደል ያልተገኘበት ሰው ነበረ፥ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። ሴም፥ ካምና ያፌት የሚባሉትን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። በዚያን ጊዜ ምድር በእግዚአብሔር ፊት የተበላሸች ነበረች፥ ምድርም ግፍን ተሞላች። እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም፥ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በምድር ላይ መንገዳቸውን አበላሽተው ነበርና፥ ምድር የተበላሸች ነበረች። እግዚእብሔርም ኖኅን አለው፦ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፥ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፥ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ለአንተ ከጎፈር እንጨት መርከብን ሥራ፥ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፥ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ አድርግ፤ ለመርከቢቱም ጣራን አብጅለት፤ ከቁመትዋም አርባ አራት ሳንቲ ሜትር ትተህ ጨርሳት፥ መርከቡ ባለ ሦስት ፎቅ እንዲሆን አድርግ፤ በጎኑም በኩል በር አድርግለት። እነሆ፥ እኔ ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት፥ በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፥ በምድር ያለ ሁሉ ይጠፋል። ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፥ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ይዘህ ወደ መርከቡ ትገባለህ። ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታስገባለህ፥ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤ ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። እንዲሁም ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።” ኖኅም እንዲሁ አደረገ፥ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}