የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 42:1-24

ኦሪት ዘፍጥረት 42:1-24 መቅካእኤ

ያዕቆብ በግብጽ እህል መኖሩን ሲሰማ፥ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ? በግብጽ እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ከመሞት መሰንበት ይሻላልና ወደዚያው ወርዳችሁ እህል ሸምቱልን” አላቸው። ከዚያም ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ወረዱ። ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን፥ ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሀት ከወንድሞቹ ጋር አላከውም። ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፥ እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ከሄዱት ሰዎች መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዥ ነበር፤ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ ደረሱ፥ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው እጅ ነሡት። ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፥ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቁጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፥ “እህል፤ ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት። ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም። በዚህ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፥ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዲህስ አይደለም፤ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤ ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።” እርሱም መልሶ፥ “አይደለም፤ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱ ግን መልሰው፥ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን፥ አንዱ ግን የለም” አሉት። ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ! ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። በሉ፥ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እስኪረጋገጥ ድረስ፥ እስር ቤት ትቆያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፥ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው። ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው። በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቈይ፥ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ። እርስ በርሳቸውም፥ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፥ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። ሮቤልም መልሶ፥ “በዚህ ልጅ ላይ፥ ‘ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው። ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለ ሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማቸው አላወቁም ነበር። ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ተመልሶ እንደገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዐይናቸው እያየ አሰረው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}