ኦሪት ዘፍጥረት 32:7-21

ኦሪት ዘፍጥረት 32:7-21 መቅካእኤ

ያዕቆብም እጅግ ፈራ ተጨነቀም፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች፥ መንጎችን እና ከብቶችን ግመሎችንም፥ በሁለት ወገን ከፈላቸው፥ “ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።” ብሎም አሰበ። ያዕቆብም አለ፦ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ ጌታ ሆይ፥ ለባርያህ ካሳየኸው ከጽኑ ፍቅርና ከታማኝነትህ ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፥ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበር፥ አሁን ግን ለሁለት ወገን የተከፈልኩ ሆንሁ። ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፥ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። አንተም፦ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ’ ብለህ ነበር።” በዚያችም ሌሊት ከዚያው ሰፈረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን አወጣ፥ ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ ዐሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ ዐሥርም እህዮችን፤ እነዚህንም መንጎቹ በየወገኑ ከፍሎ በአገልጋዮቹ እጅ አደረጋቸው፥ አገልጋዮቹንም፦ “ከእኔ ቀድማችሁ ሂዱ፥ በመንጋው እና መንጋው መካከልም እርቀት አኑሩ” አለ። የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ “ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ፥ ‘አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው?’ ብሎ የጠየቀህም እንደሆነ፥ በዚያን ጊዜ አንተ፦ ‘ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የላከው የባርያህ የያዕቆብ ነው፥ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው’ በለው።” እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዱሁ ብሎ አዘዘ፦ “ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት። ‘እንዲሁም ባርያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው’ እንድትሉት። እሱ ‘በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይቀበለኛል ፊቱንም አያለሁ’ ብሎ አስቧል።” ስለዚህ እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፥ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት እዚያው በሰፈሩበት አደረ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}