ወደ ገላትያ ሰዎች 2
2
ጳውሎስን ሐዋርያት እንደ ተቀበሉት
1 #
የሐዋ. 11፥30፤ 15፥2። ከዚያ ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ቲቶንም ከእኔ ጋር ይዤው ሄድሁ፤ 2እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም ሮጬ እንዳልሆን፥ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል፥ በመሪነታቸው ለታወቁት ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። 3ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ እንኳ፥ ግሪካዊ ቢሆንም እንዲገረዝ አልተገደደም፤ 4ይህም ወደ ባርነት ሊመልሱን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን ነጻነታችንን ሊሰልሉ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። 5የወንጌሉ እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ አልተገዛንላቸውም። 6#ዘዳ. 10፥17።መሪዎች መስለው የሚታዩት፥ በፊት ምን እንደ ነበሩ ለእኔ ለውጥ የለውም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ መሪዎች የሚመስሉት ምንም ነገር አልጨመሩልኝም፤ 7በአንጻሩ ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት እንደተሰጠው፥ እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ አዩ፤ 8ጴጥሮስን ለተገረዙት ሐዋርያ እንዳደረገው፥ እኔንም ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎኛል። 9የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ ምሰሶዎች መስለው የሚታዩ ያዕቆብ፥ ኬፋና ዮሐንስ፥ እነርሱ ወደ ተገረዙት እኛ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ የኅብረት ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ 10ድሆችን እንድናስብ ብቻ ለመኑን፤ እኔም ይህን ለማድረግ እተጋበት የነበረ ነው።
ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን እንደ ተቃወመው
11ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ሊፈረድበት ይገባ ስለ ነበር ነው። 12አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበር፤ እነሱ በመጡ ጊዜ ግን የተገረዙትን ፈርቶ ወደ ኋላ አፈገፈገ፥ ራሱንም ለየ። 13የቀሩት አይሁድ ግብዝነቱን ተከተሉ፥ በርናባስ ስንኳ ሳይቀር በግብዝነታቸው ተሳበ። 14ነገር ግን እነርሱ ከወንጌሉ እውነት ጋር በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ፥ በሁሉም ፊት ኬፋን እንዲህ አልሁት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እንደ አይሁድ ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ፥ አሕዛብ አይሁድ እንዲሆኑ ለምን ታስገድዳቸዋለህ?”
አይሁድም ሆኑ አሕዛብ በእምነት እንደሚድኑ
15እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን፤ ከኃጢአተኞች አሕዛብ አይደለንም፤ 16#መዝ. 143፥2፤ ሮሜ 3፥20፤ ሮሜ 3፥22።ሆኖም ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ በሕግ ሥራ እንዳልሆነ አውቀን፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። ሥጋ ሁሉ በሕግ ሥራ አይጸድቅም። 17ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ፥ እኛ ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ፥ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነውን? በጭራሽ አይደለም። 18ይህን ያፈረስኩትን እንደገና የማንጽ ከሆንሁ፥ እኔ ራሴ ሕግ ተላላፊ ነኝ። 19ለእግዚአብሔር እንድኖር በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼአለሁ፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ። 20ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው። 21የእግዚአብሔርን ጸጋ አልናቅሁም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነ እንግዲያውስ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነዋ!
Currently Selected:
ወደ ገላትያ ሰዎች 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ