ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እኔ ልቡንና የአገልጋዮቹን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው ምልክቶቼን እንዳሳይ ነው። ይህም በልጅህና በልጅ ልጅህ ጆሮ እንድትነግርና ግብፃውያንን እንዴት እንዳሞኘኋቸው፥ በመካከላቸው ያስቀመጥኩት ምልክቶቼም ጌታ እንደሆንኩ እንድታውቁ ነው።” ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እንዲህም አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በፊቴ እራስህን ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ እኔ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤ የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታል፥ ማንም ምድሩን ማየት አይችልም፤ ከበረዶውም ተርፎ የቀረላችሁን ሁሉ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም በሜዳ ያለ ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤ ቤቶችህም የአገልጋዮችህም ቤቶች ሁሉ የግብጽንም ቤቶች ሁሉ ይሞሉታል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ አላዩም።’” ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። የፈርዖንም አገልጋዮች፦ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? ጌታ አምላካቸውን እንዲያገለግሉት ወንዶቹን ልቀቃቸው፥ ግብጽስ እንደ ጠፋች ገና አላወቅህምን?” አሉት። ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን አመጡአቸው፦ “ሂዱ፥ ጌታ አምላካችሁን አገልግሉ፥ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። ሙሴም፦ “ወጣቶቻችን፥ ሽማግሌዎቻችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፥ በጎቻችንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ የጌታን በዓል እናደርጋለንና” አለ። እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን እናንተንና ልጆቻችሁን እለቅቃለሁ፥ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ። እንዲህ አይሆንም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱና ጌታን አገልግሉ፥ የጠየቃችሁት ይህንን ነውና።” ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው። ጌታም ሙሴን፦ “አንበጣዎቹ በግብጽ ምድር ላይ እንዲመጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ” አለው። ሙሴም በግብጽ ምድር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ ጌታም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ በነጋም ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ። አንበጣዎችም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብጽም አገር ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፥ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ ያለ አይሆንም። የምድሩንም ፊት ሸፈኑት ምድሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር በዛፉ ላይም በቡቃያው ላይም በግብጽ ምድር ሁሉ አልቀረም።
ኦሪት ዘፀአት 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 10:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች