የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1:1-14

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1:1-14 መቅካእኤ

በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፤ በክርስቶስ ኢየሱስም ለታመኑ፥ በኤፌሶን ለሚገኙ ቅዱሳን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን፥ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በሰማያዊ ስፍራ በክርስቶስ የባረከን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይባረክ። ዓለም ሳይፈጠር፥ በፍቅር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እድንሆን በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም በነጻ የሰጠን የከበረ ጸጋው እንዲመሰገን ይህን አደረገ። በእርሱም እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን፥ በደሙ ቤዛነታችንን አገኘን፤ የበደላችንም ይቅርታ ሆነ። ጸጋውንም አበዛልን። በጥበብና በአእምሮ ሁሉ፥ በክርስቶስ ለማድረግ የወደደውን የአሳቡን፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናል፤ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል፥ በዘመን ፍጻሜ እንዲሆን እንዳቀደው፥ እንደ ፈቃዱና እንደ ምክሩ ሁሉን የሚያከናውን እንደ እርሱ ዓላማ የተወሰንን በክርስቶስ በርስትነት ተቀበልን። ይኸውም በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ደግሞ ለክብሩ ምስጋና እንድንሆን ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፥ በክርስቶስም አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም ለክብሩ ምስጋና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ የርስታችን መያዣ ነው።