የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 12

12
1የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፥ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፥ 2ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፥ 3ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፥ 4የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ፥ 5ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፥ ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ፥ ሰው ወደ ዘለዓለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ፥ 6የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኩስኩስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጉድጓድ ላይ ሳይሰበር፥ 7አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። 8ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል።
9ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ እውቀትን አስተማረ፥ እርሱም ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። 10ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ።
11የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው፥ የተሰበሰቡትም ከአንድ እረኛ የተሰጡት ቃላት እንደ ተቸነከሩ ችንካሮች ናቸው። 12ከዚህም ሁሉ በላይ፥ ልጄ ሆይ፥ ተግሣጽን ስማ፥ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፥ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል።
13የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፥ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፥ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። 14እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ