የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 33

33
ሙሴ የእስራኤልን ነገድ ሁሉ እንደ ባረከ
1የጌታ ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ሕዝብ የባረከበት ቃለ ቡራኬ ይህ ነው። 2እንዲህም አለ፦
“ጌታ ከሲና ተራራ መጣ፥
በሴይርም እንደ ንጋት ተገለጠ፥
ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥
በስተቀኙም ከእሳት ነበልባል ጋር፥
ከአእላፋት ቅዱሳኑም ጋር መጣ።
3በእርግጥ ሕዝቡን ይወዳል፤
ቅዱሳኑ ሁሉ በእጁ ናቸው፤
እነርሱም በእግሮችህ ሥር ይሰግዳሉ፤
መመሪያህንም ከአንተ ይቀበላሉ።
4ይህ ሙሴ የሰጠን ሕግ፥
የያዕቆብ ጉባኤ ርስት ነው።
5የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ጋር ሆነው፥
በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ፥
እርሱ በይሹሩን ላይ ንጉሥ ነበር።”
6“ሮቤል በሕይወት ይኑር፥ አይሙት፥
ሰዎቹም በቍጥር አይነሱ።”
7ስለ ይሁዳም እንዲህም አለ፦
“ጌታ ሆይ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥
ወደ ወገኖቹም አምጣው።
እጆቹንም አጠንክርለት፤
ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋም ረዳት ሁነው።”
8 # ዘፀ. 28፥30፤ ዘፀ. 17፥7፤ ዘፀ. 17፥7፤ ዘኍ. 20፥13። ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦
“ማሳህ በተባለው ቦታ ለፈተንኸው፥
በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፥
ቱሚምህን ለሌዊ ስጠው፥
ኡሪምህም ለዚህ ቅዱስ ሰው ነው፤
9ለአንት ሲል እናቱንና አባቱን፥ ‘አላየሁም’ ላለ፥
ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥
ልጆቹንም ላላወቀ፥
ቃልህን ላከበረ፥
ቃል ኪዳንህንም ለጠበቀ።
10ሥርዓትህን ለያዕቆብ፥
ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፥
በፊትህ ዕጣንን፥
በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባሉ።
11ጌታ ሆይ፥ ሀብቱን ባርክ፥
የእጁንም ሥራ ተቀበል፤
የጠላቱን አከርካሪ ስበር፤
የሚጠሉትም ዳግመኛ አይነሡ።”
12ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፦
“በጌታ የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤
ቀኑን ሁሉ ይጠብቀዋል፤
በትከሻዎቹም መካከል ያርፋል።”
13ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥
“ምድሩ ከጌታ ዘንድ የተባረከ ይሁን፤
ከሰማያት በሚዘንበው የላቀ ስጦታ፥
ከታችም ከጥልቀት ከሚገኘው ውሃ፥
14ከፀሐዩ ሙቀት ከሚገኘው ምርጥ ፍሬ፥
ከወራት መፈራረቅ ከሚገኘው ምርት፥
15ከቀደሙትም ከጥንት ተራሮች ከፍተኛነት፥
በዘለዓለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥
16በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥
በቁጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት
በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ።
17ለላሞች በኩር ግርማ ይሆናል፥
ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፥
በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን
አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፥
የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥
የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።”
18ስለ ዛብሎን ስለ ይሳኮር ነገዶችም እንዲህ አለ፦
“ዛብሎን በመርከብ ስትጓዝ ደስ ይበልህ፤
ይሳኮርም በቤትህ ሆነህ ደስ ይበልህ።
19የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥
የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና
አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፥
በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።”
20ስለ ጋድም እንዲህ አለ፥
“ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፥
እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፥
ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል።
21በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና
የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፥
ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፥
የጌታንም ጽድቅ፥
ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።”
22ስለ ዳንም እንዲህ አለ፥
“ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፥
ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።”
23ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦
“ንፍታሌም በሞገስ ጠግቧል፥
የጌታንም በረከት ተሞልቶአል፥
ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።”
24ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦
“አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፥
በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፥ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።
25ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፥
እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።
26“ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥
በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ
እንደ ጌታ ያለ ማንም የለም።
27መኖሪያህ የዘለዓለም አምላክ ነው፥
የዘለዓለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፥
ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦
አጥፋው ይላል።
28እስራኤልም ተማምኖ፥
የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥
እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፥
ሰማያትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
29እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፥
በጌታ የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው?
እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥
የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው።
ጠላቶችህም ይገዙልሃል፥
አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ