መጽሐፈ ባሮክ መግቢያ
መግቢያ
የመጽሐፈ ባሮክ የመጀመሪያዎቹ ጥቅሶች የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ የነቢዩ ኤርምያስ ረዳት መሆኑን ያመለክታሉ (ኤር. 32፥12፤ 36፥4፤32፤ 45፥1)። መጽሐፉ የተለያዩ ጉዳዮችን ያስተናግዳል። በተለይም የእግዚአብሔር ሕዝብ ተማርኮ ወደ ባቢሎን በመወሰዱ የደረሰበትን ትልቅ መካራ ያብራራል። በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ ሁለትና በኦሪት ዘዳግም ከምዕራፍ ሃያ ስምንት እስከ ሠላሳ ሦስት እንደምናገኘው ከኃጢአት ወደ ቅጣት፥ ከቅጣት ወደ ንሥሐ፥ ከንሥሐ ወደ መመለስ እንዴት እንደሚደረስ ይዘረዝራል። በባቢሎን ምርኮ የሚገኙ አይሁዶች ምሕረትን ለማግኘት የሚያደርጉት ጸሎት፥ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ዘጠኝ እና በትንቢተ ኤርምያስ በተለያዩ ሥፍራዎች ከሚገኙ ጸሎቶች ጋር ይመሳሰላሉ። እንዲሁም ጥበብን በሰውኛ ዘይቤ የሚገልጽ ክፍል ሲገኝ፥ ስለ ጥበብ አስፈላጊነት፥ ስለ ጥበብ ምሥጢራዊነትና እንዲሁም የሙሴ ሕግ እና ጥበብ በልዩ መንገድ የተሳሰሩ ስለ መሆናቸውን ይገልጻል (ሲራክ 24)።
በመጽሐፈ ባሮክ ውስጥ ያለው የመጽናኛ ቅኔ በትንቢተ ኢሳያስ ከምዕራፍ 40-66 የሚገኙትን ቅኔዎች ይመስላል፤ ይህ ቅኔ ከባቢሎን ምርኮ ወደ ተስፋ ምድር ዳግመኛ የመመለስን መልእክት ያበሥራል። እንደዚሁም በትንቢቱ ውስጥ የጣዖት አምልኮን ያወግዛል። በተጨማሪም ጣዖታት ኃይል እንደሌላቸውና ሊፈሩ እንደማይገባቸው ያስተምራል።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
1. የኢየሩሳሌም ደብዳቤ (1፥1—3፥8)
ሀ. ታሪካዊ ዐውድ (1፥1-9)
ለ. የኃጢአት ኑዛዜ (1፥10—2፥10)
ሐ. እርዳታ ለማግኘት የሚደረግ ጸሎት (2፥11—3፥8)
2. ለጥበብ የቀረበ ውዳሴ (3፥9—4፥4)
ሀ. የጥበብ አስፈላጊነት (3፥9-23)
ለ. የጥበብ ምሥጢራዊነት (3፥24-36)
ሐ. ጥበብና የሙሴ ሕግ (3፥37—4፥4)
3. የመጽናኛ ቅኔ (4፥5—5፥9)
ሀ. ነቢዩና በባቢሎን የተማረከው ሕዝብ (4፥5-9)
ለ. ኢየሩሳሌምና ጎረቤቶቿ (4፥10-16)
ሐ. ኢየሩሳሌምና በባቢሎን የተማረከው ሕዝብ (4፥17-29)
መ. ባሮክና ኢየሩሳሌም (4፥30—5፥9)
4. የኤርምያስ ደብዳቤ (6፥1-72)
ምዕራፍ
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ መግቢያ: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ