የሐዋርያት ሥራ 2:14-47

የሐዋርያት ሥራ 2:14-47 መቅካእኤ

ነገር ግን ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው “የይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፤ “እግዚአብሔር ይላል ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁት፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዐመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፤ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና “ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፤ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።” ወንድሞች ሆይ! ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ነገር ግን እርሱ እንዳለው፦ ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፤ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ!” “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተሰበረ፤ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና፤” አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ፤” ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።