ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ “ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል፤” ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ። ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ። በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤ እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው “ሰዎች ሆይ! ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደሆነ ታውቃላችሁ። ይህም ጳውሎስ ‘በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም፤’ ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል፤ ሰምታችሁማል። ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፤ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፤ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ቁጣ ሞላባቸው “የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉም ጮኹ። ከተማውም በሙሉው ተደበላለቀ፤ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ። ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት። ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና። አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ። አይሁዳዊ ግን እንደሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ “የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ! የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው? ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል። የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመፋረጃ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ። ስለ ሌላ ነገር እንደሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል። ዛሬ ስለተደረገው ‘ሁከት ነው፤’ ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፤ ምክንያት የለምና።” ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው።
የሐዋርያት ሥራ 19 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 19:21-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች