2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:1-7

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:1-7 መቅካእኤ

ከዚህ በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ወጣ፤ ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ከእርሱ ጋር ነበሩ። እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፥ እርሱም ወደ ያቤሽ ገለዓድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት በማሳየታችሁ ጌታ ይባርካችሁ፤ አሁንም ጌታ ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ! እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፥ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።”