ጌታ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ሀብታም ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ሀብታሙ እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። እየተንከባከበ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች። ወደ ሀብታሙም ቤት እንግዳ መጣ፤ ሀብታሙ ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ የድኻውን ግልገል ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ጌታ ምስክሬ ነው! ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ ግልገሊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፥ ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በእቅፍህ አኖርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤትም ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፥ የጌታን ቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ሒታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ እኔን አቃለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የሒታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና፥ ሰይፍ ለዘለዓለም ከቤትህ አይርቅም።’ ” ጌታ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።” ከዚያም ዳዊት ለናታን፥ “ጌታን በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፥ “ጌታ ኃጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፥ የጌታ ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፥ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፥ የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን ጌታ ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ወደ ክፍሉ ገብቶም ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። የቤተሰቡ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያሰነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ አብሮአቸውም አንዳች ምግብ አልበላም። በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፥ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ። ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፥ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፥ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፥ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ጌታ ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ። አገልጋዮቹም፥ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፥ ‘ጌታ ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፥ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፥ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos