የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11

11
ዳዊትና ቤርሳቤህ
1 # 2ሳሙ. 10፥7፤ 1ዜ.መ. 20፥1። ነገሥታት ለጦርነት በሚወጡበት በጸደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን ከአገልጋዮቹና ከመላው እስራኤል ጋር አዘመተው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ራባ የተባለችውንም ከተማ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። 2አንድ ቀን ማታ፥ ዳዊት ከአልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፥ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ ውብ ነበረች። 3#2ሳሙ. 23፥39።ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ። እርሱም፥ “ይህች የኤሊዓም ልጅ፥ የሒታዊው የኦርዮን ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ። 4#ዘሌ. 15፥19።ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሮአትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርሐዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች። 5ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፥ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት። 6ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፥ “ሒታዊውን ኦርዮንን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ኦርዮንን ወደ ዳዊት ላከው። 7ኦርዮን በመጣ ጊዜም፥ ዳዊት የኢዮአብንና የሠራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። 8ከዚያም ዳዊት ኦርዮንን፥ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም የምግብ ስጦታ ላከለት። 9ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር። 10ዳዊት፥ “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮንን፥ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 11#1ሳሙ. 4፥3-4።ኦርዮም ዳዊትን፥ “ታቦቱ፥ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፥ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፥ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም” አለው። 12ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፥ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮ በዚያ ዕለትና በማግስቱ በኢየሩሳሌም ቆየ። 13በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮ በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አገልጋዮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። 14ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮ እጅ ላከለት፤ 15በደብዳቤውም ላይ፥ “ኦርዮን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ። 16ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፥ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮንን መደበው። 17የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሠራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ሒታዊው ኦርዮንም ሞተ። 18ከዚያም ኢዮአብ በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ። 19መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፥ 20ንጉሡ በቁጣ ቱግ ብሎ እንዲህ ይልህ ይሆናል፥ ‘ለመውጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለ ምንድነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል? 21#መሳ. 9፥50-54።የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤጽ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ አንተም መልሰህ፥ ‘አገልጋይህ ሒታዊው ኦርዮም ሞቷል’ ብለህ ንገረው።” 22ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደደረሰም ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው። 23መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳደን መለስናቸው። 24ከዚያም ባለፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፥ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ሒታዊው ኦርዮም ሞተ።” 25ዳዊትም፥ መልእክተኛውን፥ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፥ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን’ ” አለው። 26የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ ኀዘን ተቀመጠች። 27የሐዘኑ ጊዜ ካበቃ በኋላም፥ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት የሠራው ሥራ ጌታን አላስደሰተውም ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ