ወዳጆች ሆይ! ይህ የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው፤ በሁለቱም መልእክት ቅን ልቡናችሁን በማሳሰብ አነቃቃለሁ። ከዚህ በፊት በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል፥ እንዲሁም በሐዋርያዎቻችሁም አማካይነት ያገኛችኋትን የጌታችንንና የመድኃኒታችንን ትእዛዝ እንድታስቡ ይገባል። ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻው ዘመን እንደራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ እወቁ፤ እነርሱም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ፥ የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ፥ ሁሉ እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማያት በእግዚአብሔር ቃል መፈጠራቸውን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው አያስተውሉም። በዚህም ምክንያት ያንጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ፤ ነገር ግን አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር በዚሁ ቃል፥ እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቆያሉ። ወዳጆች ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው፥ ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ምድርም በእርሷም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል መኖር አይገባችሁም? እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ የምታፋጥኑ ሁኑ፤ ምክንያቱም ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የፍጥረት መሰረተ ነገር በእሳት ግለት ይቀልጣሉ! ነገር ግን እኛ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።
2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3 ያንብቡ
ያዳምጡ 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች