የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 6

6
የአሕዛብን አምልኮ በግዳጅ ማስፈን
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ አይሁዳውያን ከአባቶቻቸው ሕግ እንዲርቁና ሕይወታቸውንም በእግዚአብሔር ሕግ መምራቱን እንዲያቋርጡ ለማድረግ ጀሮንቲስን የተባለውን አንድ አቴናዊ ላከባቸው፤ 2የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ለማርከስና የኦሎምፖያው ዜኦስ እንዲከብር ለማድረግ በጌሪዝም ተራራ ላይ የዜኦስ የእንግዶች ጠባቂ መታሰቢያ ለማቆም አቴናውያን በጠየቁት መሠረት ወሰነ። 3የእዚህ እርኩስ ተግባር መታየት ሕዝቡ ሊሸከመው ከማለው በላይ ስቃይን አስከተለ። 4ቤተ መቅደሱ ቅጥ ባጣ ደስታና በጭፈራ ተሞላ፤ አረማውያን ከሴቶች ጋር የሚዳሩበትም ቦታ ሆነ። የተከለከለ ነገርም ይፈጽሙ ነበር። 5መሠዊያውም በሕግ በተከለከሉና በረከሱ መሥዋዕቶች ተሞልቶ ነበር፤ 6ሰንበትን ማክበር አልተፈቀደም ነበር፤ ሃይማኖታዊ በዓላትን ማሰብ፥ ሌላው ቀርቶ አይሁድ ነኝ ብሎ መናገርም አይፈቀድም ነበር። 7በንጉሡ የልደት በዓል ቀን በየወሩ እየሄዱ መብላት የማይታለፍ ግዴታ ነበር፤ የዲዮንስዩስ በዓል በሆነ ጊዜ በራስ ላይ የቅጠል ጉንጉን ደፍቶ የዲዩንስዩስን ሰልፍ መከተል ግዴታ ነበር። 8በጰጠሎማይዳ ሰዎች ምክር በአረማውየን (ግሪካውያን) ከተሞች አጠገብ የሚገኙ አይሁዳውያን እንደ አረማውያን እንዲያደርጉ አዋጅ ወጣ፤ አይሁዳውያንም ለመሥዋዕት የቀረበውን ምግብ እንዲበሉ ተገደዱ፤ 9የግሪካውያንን ልምድ የማይከተሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ ተሰጠ። በዚያን ጊዜ እንግዲህ ታላቅ ችግር የሚመጣ መሆኑ ታወቀ። 10ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን ስላስገረዙ በፍርድ ፊት አቀረቧቸው፤ በሰው ሁሉ ፊት ልጆቻቸውን እንደታቀፉ ከተማውን እንዲዞሩ ተደረጉ፤ ከዚህም በኋላ በግንቡ ላይ ወርውረው ጣሏቸው። 11ሌሎች በድብቅ የሰንበትን በዓል ለማክበር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ዋሻዎች አብረው ሄዱ። በፊሊጶስ ፊት ተከሰው በእሳት አቃጠሏቸው፤ ለቀኑ ክብር ካላቸው የእምነት ጽናት የተነሣ በእሳት ተቃጥለው ሞቱ።
በድኀንነት ጐዳና የስደት አስፈላጊነት
12ይህን መጽሐፍ የሚያነቡ ሰዎች በእነዚህ መከራዎች ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጡ አደራ እላለሁ፤ ይህ ስደት ለሕዝባችን ተግሣጽ፤ ትምህርት እንጂ ጥፋት አለመሆኑን እንዲገነዘቡ እለምናለሁ። 13ክፉ ሰዎች በክፋታቸው ረጅም ጊዜ ባለመቆየታቸው፥ ቅጣታቸውም ቶሎ የሚደርስባቸው በመሆኑ የእግዚአብሔር ታላቅ ደግነት ምልክት ነው። 14ልዑል አምላክ ሌሎችን ሕዝቦች ለመቅጣት የክፋታቸው ጽዋ እስኪሞላ ድረስ በምሕረቱ ታግሦ ይጠብቃቸዋል። ግን ከእኛ ጋር የሚያደርገው እንዲህ አይደለም፤ 15እኛን የሚቀጣን ኃጢአታችን እስከ መጨረሻ ሳይሞላ ነው። 16ስለዚህ ምሕረቱን ከቶ ከእኛ አያርቅም፤ መከራ አውርዶብን ቢገሥጸንም እኛን ሕዝቡን አይጥለንም። 17ይህን ማስታወስ ይበቃል፤ ከእዚህ በኋላ ወደ ነገራችን እንመለስ።
የአልዓዛር ሰማዕትነት
18የሕግ ሊቃውንት ከነበሩት አንዱ የሆነውንና በዕድሜ የገፋ በሁሉም ዘንድ የተከበረ አልዓዛር የተባለውን ሰው አፍ በግድ ከፈተው የዓሣማ ሥጋ እንዲበላ አስገደዱት። 19እርሱ ግን ከወራዳ ሕይወት የክብረ ሞት ይሻለኛል ብሎ 20ያልተፈቀደ ነገርን መቅመስ እንደሚቃወሙ ሰዎች ሁሉ በአፉ ውስጥ የገባውን ቁራጭ ሥጋ በመትፋት ከሕይወት ይልቅ ሞትን መረጠ። በገዛ ፈቃዱ ወደሚያሠቃዩበት ቦታ ሄደ። 21በበዓሉ ላይ የነበሩ ሰዎች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ አልዓዛርን ያውቁት ስለ ነበር ገለል አደረጉትና ለመኑት፤ እርሱ መብላት የሚችለውን ሥጋ ከገዛ ቤቱ እንዲያስመጣና በንጉሡ እንደ በላ የታዘዘውን ሥጋ አሥመስሎ እንዲበላ መከሩት፤ 22እንዲህ በማድረግ ከሞት ስለሚድን በቀድሞ ፍቅራቸው ምክንያት ይህን መከሩት። 23እርሱ ግን ለዕድሜው የተስማማ የክብር ሥራ ለመሥራት ፈልጐ ከልጅነቱ ጀምሮ ሳያወላውል የኖረ፤ ይልቁንም በተቀደሰው የእግዚአብሔር ሕግ የጸና፤ በተከበረ ሸምግልናውና ሽበቱ ሥልጣን ያለው መሆኑን አውቆ ሳትዘገዩ ግደሉኝ ሲል መልስ ሰጠ፤ 24እንዲህም አለ፥ “በእኛ ዕድሜ በማስመሰል መሥራት አይገባም፤ አለበለዚያ ወጣቶች ለዚች ዕድሜው ሲል አልዓዛር በዘጠና ዓመት ዕድሜው የሌሎችን አገሮች ሕይወት ተከተለ ብለው ያምናሉ፤ 25ታዲያ እነርሱም ለብዙ ጊዜ በማይጠቅመኝ በዚህ ወራዳ ድርጊት የተነሣ አኔን በመመልከት ከሚከተሉት ቀና ጐዳና ሊወጡ ይችላሉ። በስተርጅና ላተርፍ የምችለው ነገር ቢኖር እራሴን ማሳደፍና ክብሬን ማዋረድ ብቻ ነው። 26አምላክ እጅ አላመልጥም። 27አሁን ምንም ሳልፈራ ሕይወቴን አሳልፌ ብሰጥ ለሽምግልናዬ የተገባሁ ሆኜ እገኛለሁ፤ 28ይህን በማድረጌ ወጣቱ ትውልድ በደግነት፥ በክብርና በጉጉት ስለቅዱሳት ሕግጋት ሲል ሞትን በድፍረት ይጋፈጥ ዘንድ የእኔን አብነት ይከተላል”። 29ይወስዱት የነበሩ ሰዎች በፊት በመልካም ዐይን ይመለከቱት የነበሩ ሐሳባቸውነ ለውጠው በክፉ ዐይን ተመለከቱተ፤ ምክንያቱም የተናገረው ንግግር እንደ ዕብደት መስሎ ታያቸው። 30እርሱ ግን ሲደበደብ ሳለ ከመሞቱ በፊት እየሳቀ እንዲህ አለ፥ “ቅዱስ ዕውቀት ያለው አምላክ ከሞት ማምለጥ ስችል በሥጋዬ የሚያሠቃዩኝን ጅራፎች ታግሼ መቀበሌን ያውቃል፤ ነገር ግን ነፍሴ ይህን ሁሉ ስቃይ በመቀበል ትደሰታለች”። 31በእንደዚህ ዓይነት ነው ይህ ሰው በሞቱ ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለሕዝቦች ሁሉ የጥንካሬ ምሳሌና የብርታት ማስታወሻ ትቶ ያለፈው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ