2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 4
4
በአንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ ዘመን የግሪካውያን ሥርዓት ኘሮፖጋንዳ እና ስደት
የቤተ መቅደሱ አስተዳዳሪ፥ የስምዖን ክፉ ተግባር
1ግምጃ ቤቱን ለማስወረስ የተናገረውና ሀገሩን የከዳ፥ ያ ስምዖን በኦንያ ላይ ክፉ መናገሩን ቀጠለ፤ ጌልዮድሮስን ያስደበደበና እነዚያን መከራዎች ያወረደበት እርሱ ነው እያለ ይናገር ነበር። 2የከተማዋ መልካም አድራጊ፥ የወንድሞቹ ጠባቂ፥ እርሱን ለመክሰስ ደፈረ፥ 3ጥላቸውም እያደገ ሄዶ በሰምዖን የተቀጠሩ ወኪሎች ግድያዎችን እስከ መፈጸም ደረሱ፤ 4ኦንያ ይህ ጥላቻ ምንኛ የከፋ መሆኑንና የቀለሲርያና የፊኒቄስ አስተዳዳሪ የሆነው የምነስጤዬ ልጅ አጶሎንዮስ የስምዖንን ክፋት እያበረታታ የሚሄድ መሆኑንም በማየት 5ወደ ንጉሡ ሄዳ፤ የሄደውም የሀገሩን ሰዎች ለመክሰስ ሳይሆን የሕዝቡን ሁሉ የጋራና የግል ጥቅማቸውን በመፈለግ ነው፤ 6ከእንግዲህ ወዲህ ያለ ንጉሥ ውሳኔ በአስተዳደሩ ውስጥ ሰላምን ማግኘት እንደማይቻልና ስምዖንም እብደቱን እንደሚያቆም ስለተገነዘበም ጭምር ነው።
ሊቀ ካህናት ኢያሶን የግሪካውያንን ሥርዓት አስተዋወቀ
7ሴሌውከስ ከሞተ በኋላ ኤጲፊንዮስ አንጥኩስ መንግሥቱን በያዘ ጊዜ የኦንያም ወንድም ኢያስን የሊቀ ካህንነትን ሹመት ተመኘ፤ 8ወደ ንጉሡ ሄደና ሦስት መቶ ስለሳ የብር መክሊት እንደሚሰጠውና ሰማንያ መክሊትም ሌላ ጊዜ እንደሚጨምርለት ቃል ገባለት። 9ጅምናሲዩም እና የወጣት ማእከል ቦታ ለመሥራትና የኢየሩሳሌም አንጾኪያውያን ለመመዝገብ ሥልጣን የሰጠው እንደሆነ አንድ መቶ ሃምሳ መክሊት በተጨማሪ እንደሚሰጠውም ቃል ገባለት፤ 10ንጉሡ እሺ አለውና ኢያሶን ሥልጣኑን በጨበጠ ጊዜ ወዲያውኑ የገዛ ራሱን ሕዝብ ሥርዓት አስለውጦ እንደ ግሪካውያን እንዲኖሩ አደረጋቸው። 11ነገሥታት በመልካም ፈቃዳቸው ስለ ዮሐንስ ሲል ለአይሁዳዊያን የሠሩትን ሥርዓት አፈረሰ፤ ዮሐንስ የኤውጶለም አባት ነው፤ ኤውጶለም ከሮማውያን ጋር የወዳጅነትና የስምምነት ውል ለመዋዋል ወደ ሮም የተላከ ሰው ነው። ኢያሶን እንዲሁም የሀገሩን ሥርዓት አፍርሶ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጻረሩ ሥርዓቶች አስገባ። 12በቤተ መቅደስ ተራራ አጠገብ የሚገኘው ምሽግ ግርጌ ጅምናሲዩም እስከሚቋቋም ደረሰ፥ ምርጥ የሆኑ ታዋቂ ስፖርተኞችንም ልብስ አልብሶ ወደ እዚያ አስገባቸው። 13አምላኩን የከዳ እና እውነት ሊቀ ካህንም ባለመሆኑ ኢያሶን ለትዕቢቱ ገደብ አልነበረውም፤ የግሪካውይንን ሥርዓት የማስፋፋቱ ተግባር ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ 14ካህናት እንኳ የመሠዊያውን አገልግሎት ለመፈጸም አይተጉም፤ ቤተ መቅደሱን ንቀው መሥዋዕቶቹን ችላ ብለዋል፤ ልክ ደወል ሲደወል በሕግ ወደ ተከለከው ዘይት በማደሉ ጨዋታ ለመሳተፍ ይሽቀዳደማሉ። 15የሀገራቸውን ክብር ንቀው የአረማውያን ክብር ንቀው የአረማውያንን ክብር መረጡ። 16በዚህ ምክንያት ብዙ ችግር ወደቀባቸው፤ ሥርዓታቸውን መከተልና እነርሱን መምሰል ፈለጉ፤ እነርሱ ግን ጠላቶቻቸውና ገራፊዎቻቸው ሆኑ። 17የአምላክን ሕግ መጣስ በቀላሉ የሚታለፍ ነገር አይደለም፤ መጪው ዘመን እንደሚያሳየው የእግዚአብሔርን ቃል መሻር እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። 18በጢሮስ በየአራቱ ዓመት ንጉሡ ባለበት የማከበር ታላቅ የስፖርት በዓል ነበር፤ 19ርኩሱ ኢያሶን ከኢየሩሳሌም የአንጾኪያ ሰዎችን እንደ መልእክተኞች አድርጐ ወደዚያ ላካቸው፤ እነርሱ ለህርቆል መሥዋዕት ሊባክን አይገባውም፤ ይልቁንም ለሌሎች ወጪዎች መቀመጥ አለበት ብለው ወሰኑ። 20ለህርቆል መሥዋዕት እንዲሆን ብሎ ኢያሶን የላከው ብር ይዘውት በሄዱት ሰዎች አሳሳቢነት ለመርከቦች ማሰሪያ ዋለ። አንጥዮኩስ ኤጲፋኒዮስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ 21የምነስጢዩስ ልጅ አጶሎንዮስ በንጉሥ ፊልመትሮስ የጋብቻ በዓል ላይ እንዲገኝ ወደ ግብጽ ተላከ፤ አንጥዮኩስ ንጉሥ ፊልመትሮስ እርሱን በሚመለከቱ ነገሮች ሁሉ በጠላትነት ዐይን እንደሚያየው በማወቅ ስለ ደህንነቱ ማሰብ ጀመረ። በዚህም ምክንያት ወደ ኤዮጴ ደረሰና ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። 22ኢያስንና የከተማው ሰዎች በክብር ተቀበሉት። በችቦ ብርሃንና በዕልልታ አስገቡት። ከዚህ በኋላ ሠራዊትን ወደ ፌንቄስ አዘመተ። መነላዎስ ሊቀ ካህናት ሆነ 23ከሦስት ዓመት በኋላ ኢያሶን የዚያን የስምዖን ወንድም መነላዎስን ለንጉሡ ገንዘብ እንዲወስድና አጣዳፊ ስለሆኑት ጉዳዮች እንዲነጋገር ላከው። 24መነላዎስ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንደ ባለ ሥልጣን እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ ተናግሮ የሊቀ ካህንነት ሹመት እንዲሰጠው አደረገ፤ ከኢያስን አብልጦም ሦስት መቶ የብር መክሊት ሰጠው። 25ከነጉሡ የተሰጠውን የሹመት ደብዳቤ ይዞ ተመለሰ፤ ይሁን እንጂ ለሊቀካህንነት የሚያበቃው ምንም ዓይነት ችሎታ አልነበረውም፤ የጨካኝነት መዓቱን፥ የአውሬነት ቁጣውን ከማሳየት በቀር ሌላ ነገር አያውቅም። 26ኢያሶን የወንድሙን ሹመት በግፍ እንደወሰደ እንዲሁም የእርሱም ሹመት በሌላ ሰው ተወሰደበትና ወደ አምናቡያን አገር ተሰዶ ሄደ። 27መነላዎስ ግን ሥልጣንን ጨበጠ፤ ሆኖም እስጣለሁ ብሎ ለንጉሡ ቀል የገባለትን ገንዘብ አይሰጥም ነበር። 28ነገር ግን የምሽጉ አዛዥ ነበር። ስለዚህ ሁለቱም ተጠርተው ወደ ንጉሡ ሄዱ። 29መነላዎስ ለሊቀ ካህንነቱ ሠራ ወንድሙን ሊሲኰማስን ተካ፤ ሶስትራትም የቆጅሮሳውያን ሹም የነበረውን ክራቴምን ተካ። ኦንያ ተገደለ 30አገራቸው የንጉሥ ዕቁባት ለሆነችው ለአጥናዩኪዶ ስለተሰጠባቸው የተርሲስና የማሎ አገር ሰዎች ከዚህ በኋላ ሁከት አስነሡ። 31ስለዚህ ንጉሡ ከሹማምንቱ አንዱን አንድሮኒቆስን በቦታው ተክቶ ሁከቱን ለማረጋገጋት በፍጥነት ሄደ። 32መነላዎስ ጥሩ አጋጣሚ እንደመጣለት ተረድቶ የቤተ መቅደሱን የወርቅ ዕቃዎች ወሰደና ለአንድ ሮኒቆስ ሰጠ፤ ሌሎችንም ዕቃዎች ለጤሮስና በአካባቢው ለሚገኙ አገሮች ሸጠ። 33ኦንያ ይህን ነገር ካረጋገጠ በኋላ በአንጾኪያ አጠገብ በምትገኝ በተጠበቀች ከተማ በጻፍን ሆኖ ተግሣጹን አሰማው። 34ስለዚህ መነላወስ አንድሮኒቆስን ብቻውን ገለል አድርጐ ኦንያን እንዲገድለው መከረው፤ አንድሮኒቆስም ወደ ኦንያ ሄዶ በተንኰል በማታለል፥ ቀኝ እጁን ዘርግቶ በመማል ምንም እንኳ ቢጠራጠር ከተሸሸገበት ቦታ እንዲወጣ አደረገውና ፍትሕን በመጣስ ወዲያውኑ አስገደለው። 35በዚህ ምክንያት አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች አገሮች ሰዎችም ፍትሕ በጐደለበት በዚህ ሰው ግድያ እጅግ በጣም ተቆጡ። 36ንጉሡ ከቂልቅያ በተመለሰ ጊዜ በከተማው የሚገኙ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ይህን የዓመፅ ሥራ አብረው በመንቀፍ ወደ ንጉሡ ቀርበው ያለ ፈርድ የተፈጸመውን ግድያ ገለጹለት፤ 37አንጥዮኩስ በልቡ አዝኖና ራርቶ የሟቹን ጥበብና ደግነት በማስታወስ እንባውን በማፈሰስ አለቀሰ። 38በጣም ተናዶ ወዲያውኑ ከአንድሮኒቆስ ክብሩን ገፈፈ፤ ልብሶቹንም ቀደደበት፤ በኋላም በከተማው ዙርያ እየዞሩ በኦንያ ላይ ግድያ እስከፈጸመበት ድረስ እንዲወስዱት አድርጐ ይህን ነፍሰ ገዳይ አስገደለው፤ አንድሮኒቆስ በእግዚአብሔር ተቀስፎ እንዲህ የተገባ ቅጣቱን አገኘ። የሊሲማቆስ በዓመፅ መገደል 39ሊሲማቆስ ከመነላዎስ ጋር በመስማማት ብዙ የቤተ መቅደስ ዕቃዎችን ሰርቆ ወስዶ ነበር፤ የዚህ ነገር ወሬ በውጭ ስለ ተሰማ ሕዝቡ በሊሲማቆስ ላይ ተነሣበት፤ እርሱ ብዙ የወርቅ ዕቃዎችን አውጥቶ አጥፍቶ ነበር። 40ሕዝቡ በጣም ተቆጥቶ በተነሣበት ጊዜ ሊስማቆስ ሦስት ሺህ ወታደር አሰልፎ፥ አንድ የጦር አለቃ ሾሞ ያልተገባ ውጊያ አደረገ፤ ይህ የጦር ሹም ስሙ አውራኖስ የተባለ በዕድሜ የገፋና ዕብድ መሣይም ነበር። 41ውጊያው የተሠነዘረባቸው ከሊሲማቆስ መሆኑን አውቀው አንዳንዶቹ ድንጋይ፥ ሌሎቹ ዱላ ይዘው ለመዋጋት ተነሡ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እዚያ የነበረውን አመድ በእጆቻቸው እያፈሱ በሊሲማቆ ሰዎች ለይ በመበተን ተዋጉ። 42በዚህ ዓይነት ብዙዎችን አቆሰሉ፤ አንዳንዶቹን ገደሉ፤ የተቀሩትንም አባረሩ፤ የቤተ መቅደሱን ዕቃዎች የወሰደውን ሊሲማቆስንም በቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት አጠገብ ገደሉት።
መነላዎስ በገንዘብ ነጻ ወጣ
43በእነዚህ ነገሮች መነላዎስ ለፍርድ ቀረበ፤ 44ንጉሡ ወደ ጢሮስ በመጣ ጊዜ ከሽማግሌዎች ምክር ቤት የተላኩት ሦስት ሰዎች ለንጉሡ ክሳቸውን አቀረቡ። 45መነላዎስ እንደሚረታ አውቆ ለጰጠሎሜዮስ ልጅ ለይሪመን ከንጉሡ እንዲያማልደው ብሎ ብዙ ወርቅ ሰጠው። 46ስለዚህ ጰጠሎሜዮስ ንጉሡ ነፋስ እንዲቀበል ብሎ ወደ ውጪ ወሰደውና መክሮ ፍርድ እንዲለውጥ አደረገው። 47በዚህ ዓይነት ንጉሡ ብዙ ክፋት የሠራው መነላዎስን ከክሱ ነጻ አድርጐ ለቀቀው፤ ምስኪኖቹ ግን ሞት ፈረደባቸው፤ እነዚህ ምስኪን ሰዎች ጨካኞች ለተባሉት ለሲጢ ሰዎች እንኳ አቤት ቢሎ ኖሮ ነጻ በተለቀቁ ነበር። 48ከተማዋንና አካባቢዎችዋን፥ የተቀደሱ ዕቃዎችንም ለማዳን የተከላከሉት ሰዎች የግፍ ፍርድ ወደቀባቸው። 49የጢሮስ ሰዎች እንኳ በጣም አዝነውላቸው በደንብ እንዲቀበሩ አደረጓቸው፤ 50መነላዎስ ግን በባለሥልጣኖች ገንዘብ ወዳድነት ምክንያት በክፋቱ እየገፋ ሄዶ ተሾመ፤ ሥልጣን አገኘ፤ ለሀገሩ ሰዎችም ትልቅ ጠላት ሆነ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ