2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 15
15
ኒቃኖር በእግዚአብሔር ላይ ጸያፈ ቃል ተናገረ
1ኒቃኖር ይሁዳና የእርሱ ሰዎች በሰማርያ አካባቢ እንደሚገኙ ሰምቶ በሰንበት ቀን ያለ ምንም ፍርሃት ጦርነት ሊገጠማቸው ውሳኔ አደረገ፤ 2ተገድደው ይከተሉበት የነበሩ አይሁዳውያን እንዲህ አሉት፥ “በእንዲህ ዓይነት አረመኔነትና ጭካኔ አታጥፋቸው፤ ሁሉን የሚያይ አምላክ ያከበረውንና የቀደሰውን ቀን አክብር”። 3ይህ ባለ ሦስት ቀለሙ ክፋና ጨካኝ ሰው ግን፥ “ለመሆኑ ሰንበት ቀን እንዲከበር ያዘዘ በሰማይ ጌታ አለን?” ሲል ጠየቀ፤ 4“በሰባተኛው ቀን እንዲከበር ትእዛዝ የሰጠ የሰማየ ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው” ሲሉ መለሱለት፤ 5እርሱም “እኔም እኮ የምድር ጌታ ሆኜ ሰዎች የጦር መሣሪያ እንዲያነሡና ንጉሡን እንዲያገለግሉ አዛለሁ” በማለት አሾፈ፤ ሆኖም የጭካኔ እቅዱን በሥራ ላይ ማዋል አልቻለም።
ይሁዳ ለሰዎቹ ንግግር አደረገ፥ ሕልምም አየ
6ኒቃኖር በታላቅ ትዕቢት ተነሣሥቶ ይሁዳንና የእርሱን ሰዎች በማሸነፈ የአሸናፊነት ምልክት ማቆመ ፈለገ፤ 7ይሁዳ መቃቢስ በበኩሉ የማይበገር እምነት ነበረው፤ ከእግዚአብሔር እርዳታ እንደሚያገኝ ሙሉ ተስፋ ነበረው። 8የአሕዛብ ሰዎች ጥቃት ቢሰነዝሩባቸው እንዳይፈሩ ነገር ግን ቀደም ሲል ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን እርዳታ እንዲያስታውሱ አሳሰባቸው፤ በኃያሉ አምላክ ድል የሚመጣላቸው መሆኑን እንዲጠባበቁም መከራቸው። 9የሙሴን ሕግና ነቢያትን በመጥቀስ አበረታታቸው፤ ከዚህ ቀደም ያደረጉትን ጦርነትም በማስታወሰ አዲስ ጥንካሬ አሳደረባቸው። 10በዚህ ዓይነት ከነቃቃቸው በኋላ አረማውያን ሕግ የማይጠብቁና መሐላቸውንም የሚያፈርሱ መሆናቸውን አስረድቶ ምክሩን አቆመ።
11በጦርና በጋሻ ብቻ ሳይሆን ያስታጠቃቸው እያንዳንዳቸውን በመልካም ምክሩም አበረታታቸውና አንድ የታመነ ሕልም እንዲያውም እውነተኛ ራእይ ማየቱን አውርቶላቸው ሁሉንም አስደሰታቸው። 12ያየውም ራእይ እንዲህ ነበር፥ አንድ በፊት ሊቀ ካህናት የነበረ የዋህና ደግ ሰው፥ መልኩ ግሩም፥ ሁኔታው ያማረ፥ አነጋገሩ መልከም የሆነ፥ ከልጅነቱ ጀምሮ በጽድቅ ሥራ የተጠመደ ስለ መላው የአይሁድ ሕዝብ እጆቹን ዘርግቶ ሲጸልይ አየ፤ 13ቀጥሎም እንዲሁ አንድ ሽበታም ሰው እጅግ ክቡር የሆነ፥ ድንቅ የሆነ ግርማ ያለውና እጅግ ውብ የሆነ ሰው ለይሁዳ ታየው። 14ኦንያ እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ይህ ሰው ወንድሞቹን የሚወድ ነው፤ ስለሕዝቡና ስለ ቅድስቲቱ ከተማ ብዙ ጸሎት የሚያደርግ የእግዚአብሔር ነቢይ ኤርምያስ ነው”፤ 15ኤርምያስ በቀኝ እጁ የወርቅ ሰይፍ ለይሁዳ አቀረበለትና፥ 16“እንካ ይህን የተቀደሰ ሰይፍ የአምላክ ስጦታ ነው፤ በእርሱ ጠላቶች ትጥላለህ አለው።”
የተዋጊዎቹ ዝግጅት
17ይሁዳ በተናገራቸው መልካምና በጀግነት በሚያነሣሡ፥ ለወጣቶችም በወንድነት ለመዋጋት ብርታት የሚሰጡ ቃላት ተጠናክረው አይሁዳውያን በሠፈር መቆየት ሳይሆን በድፈረት ወደ ጦርነት ለመሄድና በኃይል ለመዋጋት ቆረጡ፤ ምክንያቱም ከተማቸው፥ ሃይማኖታቸውና ቤተ መቅደሳቸው በአደጋ ላይ በመገኘታቸው ነው። 18ስለ ሴቶችና ስለ ልጆች፥ ስለ ወንድሞችና ስለ ዘመዶች እምብዛም አልተጨነቁም ነበር፤ ያሳሰባቸውና የስፈራቸው የቤተ መቅደሱ ጉዳይ ነበር። 19በከተማው ውስጥ የነበሩት ሰዎች ጭንቀት ትንሽ አልነበረም፤ ጭንቀታቸው በመካሄድ ላይ ስላለው ጦርነት ነበር።
20ሁሉም እንግዲህ የነገሩን ፍጻሜ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ጠላቶች ተሰብስበው ሠራዊታቸውን ለጦርነት በማሰለፍ ላይ ነበሩ፤ ዝሆኖቹን በምቹ ቦታ አድርገዋቸው ነበረ፤ ፈረሶችም በጐን በኩል ነበሩ። 21ይሁዳ መቃቢስ የወታደሮቹን መቃረብ፥ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ዝግጅትና የዝሆኖቹን አስፈሪነት ተመለከተ። እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ታምራትን ለሚያደርገው አምላክ ልመና አቀረበ፤ ምክንያቱም ማሸነፍ የሚቻለው በጦር መሣሪያ አለመሆኑንና ድል የሚገኘው በአምላክ ውሳኔና እሱ ድልን ለሚገባቸው ሰዎች ሲሰጥ ብቻ መሆኑን አወቀ። 22ልመናውም እንዲህ ነበር፥ “አንተ ጌታ ሆይ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረው በሕዝቅያስ ዘመን መልአክህን ልከሀል፤ ከሰናክሬም ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን መልአኩ ገድበሏቸዋል። 23እንዲሁም አሁን የሰማያት ጌታ ሆይ ፍርሃትንና መንቀጥቀጥን የሚያወርድባቸው መልአክ ላክልን። 24የተቀደሰውን ሕዝብህን ለመውጋት እየተሳደቡ የመጡትን ሰዎች ታላቁ ክንድህ ይደቁሳቸው”። ጸሎቱን እዚህ ላይ አቆመ።
የኒቃኖር መሸነፍና መሞት
25የኒቃኖር ወታደሮች መለከት እየነፉና የጦር መዝሙር እየዘመሩ ወደፊታቸው በሚገሰግሱበት ጊዜ፥ 26የይሁዳ ሰዎች በልመናና በጸሎት ከጠላቶቻቸው ጋር ጦርነት ገጠሙ። 27በእጃቸው እየተዋጉና በልባቸው እየጸለዩ ከሠላሳ ሺህ ሰዎች የማያንሱ ገድለው ጣሉ፤ የእግዚአብሔርም መገለጽ በጣም አስደሰታቸው። 28ጦርነቱን ፈጽመው በደስታ ሲመለሱ ኒቃኖር ከጦር መሣሪያው ወድቆ አገኙትና አወቁት።
29ከእዚህ በኋላ በአባቶቻቸው ቋንቋ ታላቁን ጌታ እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል ይሉ ጀመር፤ 30በመጀመሪያ ደረጃ ሥጋውንና ነፍሱን ስለ ሀገሩ የሠዋው የጦር መሪ የሀገሩን ሰዎች በጣም ያፈቀረው ይሁዳ የኒቃኖርን ራሱንና ክንድን እስከ ትከሻው ቆርጠው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲወስዱ አዘዘ። 31እርሱ ራሱም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደና የሀገሩን ሰዎች ሰብስባ፥ ካህናትንም በመሠዊያው ፊት አቆመ፤ በምሽጉ ውስጥ የነበሩትነም እንዲጠሩ አዘዘ። 32የዚያን የክፉ ሰው የኒቃኖርን ራስና ሁሉን በሚችል አምላክ ቤተ መቅደስ ላይ ያ ተሳዳቢ የዘረጋውን እጁን አሳየ፤ 33የዚያን የክፉ ሰው የኒቃኖርን ምላስ ጐምዶ እየቆራረጠ ለወፎች እንዲሰጥና ስለ ፈጸመው በደል ሁሉ ዋጋው ይሆን ዘንድ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት እንዲሰቀል አዘዘ። 34ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደ ሰማይ ለክቡር ጌታ ምስጋና አቀረቡ፥ “ቅዱስ ቦታውን ከመርከስ የጠበቀ አምላክ ይባረክ” አሉ።
35ይሁዳ የእግዚአብሔርን እርዳታ ግልጽ አድርጐ የሚያሳይ ምልክት የሆነውን የኒቃኖርን ራስ በመሽጉ ላይ አሰቀለው። 36ሁሉም በአንድ ቃል አብረው ይህ ቀን ሳይከበር እንዳይታለፍ ሲሉ ወሰኑ፤ ቀኑም በአረማይክ ቋንቋ (በሶሪያ) አዳር የተባለው የዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ አንደኛው ቀን የመርዶክዮስ ቀን ነው።
የጸሐፊው መደምደሚያ
37የኒቃኖር ነገር እንዲህ ተፈጸመ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዕብራውያን ከተማዋን ይዘው ቀሩ። እኔም ሥራዬን በዚሁ ፈጸምሁ። 38ዜናው መልካምና የተሳካ ሆኖ ከተገኘ የእኔም ምኞት ይኸው ነው፤ ጽሑፉ ዋጋ ቢስ ከሆነና ለጥቅስ ካልበቃ አቅሜ የፈቀደው ይሄን ብቻ ነው። 39የወይን ጠጅ በደረቁ ቢጠጣ እንደሚጐዳ ሁሉ ውሃም ለብቻው አይወሰድም፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ ከውሃ ጋር በተቀላቀለ ጊዜ ጣፋጭና የደስታን ስሜት የሚፈጥር ነው። እንደዚሁ ሁሉ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በተገቢው መልክ የማቅረብ ችሎታ መጽሐፉን ለሚያነቡ ሁሉ የግንዛቤን ደስታ ይሰጣል። እኔም ጽሑፌን በዚህ አበቃለሁ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ