2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32:24-33

2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32:24-33 መቅካእኤ

በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፥ ወደ ጌታም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፥ ምልክትም ሰጠው። ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፥ ልቡም ኰራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቁጣ ሆነ። ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኩራት ራሱን አዋረደ፥ የጌታም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም። ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀበትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቁና ለሽቶው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ። ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንሰሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። ጌታም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፥ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፥ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ። ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለተደረገው ተአምራት ለመጠየቅ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ ጌታ እርሱን ለመፈተንና በልቡ ያለውን ሁሉ ለማወቅ ሲል ተወው። የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥርዓት አደረጉለት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።