1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6:6-19

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6:6-19 መቅካእኤ

ነገር ግን ከሃይማኖት ጋር ያለኝ ይበቃኛል ማለት ትልቅ ጥቅም የሚያስገኘ ነው፤ ወደዚህ ዓለም ምንም ይዘን አልመጣንምና፥ ከዚህም ዓለም ይዘነው የምንሄደው ምንም ነገር የለም፤ ነገር ግን ምግብና ልብስ ካሉን እነዚህ ይበቁናል። ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ለመሆን የሚፈልጉ በፈተናና በወጥመድ፥ ሰዎችንም በጉስቁልናና በጥፋት ወስጥ በሚያሰጥሙአቸው ከንቱና ጎጂ በሆኑ በብዙ ምኞቶች ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፤ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ ከእምነት ፈቀቅ በማለት መንገዳቸውን ስተው ሄደዋል፥ በብዙም ሥቃይ ራሳቸውን ወግተዋል። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አንተ ግን ከእነዚህ ነገሮች ሽሽ፤ ጽድቅን፥ እግዚአብሔርን መምሰልን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ መጽናትን፥ የዋህነትን ግን ተከተል። መልካሙን የእምነት ውጊያ ተዋጋ፤ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የመሰከርህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ያዝ። ለሁሉ ነገር ሕይወት በሚሰጠው በእግዚአብሔርና በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ይህን ትእዛዝ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ጠብቅ፤ የተባረከና ብቻውን ገዢ የሆነ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ይህን ነገር ተገቢ በሆነው በራሱ ጊዜ ይገልጠዋል። እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ እርሱን ከቶ ማንም አላየውም፤ ማንም ሊያየውም አይችልም፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤ አሜን። በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑትን ሰዎች እንዳይታበዩ በሚያልፍም ባለጠግነት ላይ ሳይሆን እንድንደሰትበት ሁሉን አትረፍርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር ላይ ተስፋ እንዲያደርጉ እዘዛቸው። መልካምን ያድርጉ፥ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች በመሆን ለመለገስና ለማካፈል የተዘጋጁ ይሁኑ፤ በዚህ ዓይነት እውነተኛውን ሕይወት እንዲይዙ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ ያከማቻሉ።