የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4

4
ስለ ሐሰተኞች መምህራን
1መንፈስ ግን በግልጥ እንዲህ ይላል በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት ትኩረት በመስጠት እምነትን ይክዳሉ፤ 2ይህም ትምህርት ኅሊናቸውን በጋለ ብረት በማቃጠል አደንዝዘው ውሸትን በሚናገሩ ግብዞች በኩል የሚሰጥ ነው፤ 3እነርሱም መጋባትን ይከለክላሉ፤ አምነውም እውነትን ላወቁት፥ ከምስጋና ጋር እግዚአብሔር የፈጠረውን ምግብ ከመቀበል እንዲቆጠቡ ያዝዛሉ። 4ዳሩ ግን እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ በምስጋናም ከተቀበሉት ምንም የሚጣል ነገር የለም፤ 5በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
የክርስቶስ መልካም አገልጋይ ስለ መሆን
6ይህን ትእዛዝ ለወንድሞች ብታሳውቅ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃላት እየተመገብክ ያደግህ፥ የክርስቶስ ኢየሱስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። 7ነገር ግን ከረከሰው ከዚህ ዓለም አፈ ታሪክና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ። እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አለማምድ። 8ሰውነትን አካላዊ እንቅስቃሴ ማለማመድ መጠነኛ ጠቀሜታ ቢኖረውም እንኳ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣውን ሕይወት የተስፋ ቃል ስላለው፥ ለሁሉ ነገር ይጠቅማል። 9ይህ ቃል የታመነና ሁሉ ሰው ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ 10ለዚህም እንደክማለን እንታገላለንም፤ ምክንያቱም ሰውን ሁሉ በተለይም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስላደረግን ነው።
11እነዚህን ነገሮች እዘዝ፤ አስተምርም፤ 12ማንም ወጣትነትህን አይናቀው፤ ይልቅስ በንግግር፥ በኑሮ፥ በፍቅር፥ በእምነት፥ በንጽሕና፥ ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን። 13እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝቡ በማንበብ፥ በመምከርና በማስተማር ትጋ። 14ሽማግሌዎች እጃቸውን በአንተ ላይ የጫኑ ጊዜ በትንቢት የተሰጠህን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል። 15እድገትህ በሁሉ ሰው ፊት እንዲገለጥ እነዚህን ነገሮች በጥንቃቄ በሥራ ላይ አውል፤ ለእነርሱም ራስህን ሙሉ በሙሉ በመስጠት ትጋ። 16ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ነገሮች ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንና የሚሰሙህን ታድናለህ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ