1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5
5
1ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ 2#ማቴ. 24፥43፤ ሉቃ. 12፥39፤ 2ጴጥ. 3፥10።የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ የሚመጣ መሆኑን እናንተው ራሳችሁ በጥንቃቄ አውቃችኋልና። 3እነርሱም፦ “ሰላምና ደኅንነት ነው” በሚሉ ጊዜ ምጥ እንደ ያዛት እርጉዝ ሴት ድንገተኛ ጥፋት በእነርሱ ላይ ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም። 4ወንድሞች ሆይ! እናንተ ግን ቀኑ እንደ ሌባ እንዳይመጣባችሁ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም፤ 5እናንተ ሁላችሁም የብርሃን ልጆች፥ የቀንም ልጆች ናችሁና፤ ሆኖም እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም። 6እንግዲያስ እንንቃ፥ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። 7የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ 8#ኢሳ. 59፥17፤ ኤፌ. 6፥13-17።እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን በመጠን እንኑር፤ የእምነትንና የፍቅርንም ጥሩር፥ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንልበስ፤ 9እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳንን እንድናገኝ እንጂ ለቁጣ እንድንሆን አስቀድሞ አልመረጠንም። 10የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንድንኖር ስለ እኛ ሞተ። 11ስለዚህ እናንተ በእርግጥ እያደረጋችሁት እንዳላችሁት፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ አንዱም ሌላውን ያንጸው።
የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ
12ወንድሞች ሆይ! በእናንተ መካከል የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም እንድታውቁ፥ 13ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ እንድታከብሩአቸው እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። 14ወንድሞች ሆይ! እንመክራችኋለን፤ ሰነፎችን ገሥጹ፤ ፈሪዎችን አጽኑ፤ ደካሞችን እርዱ፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። 15ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ እንዲሁም ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ። 16ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ 17ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ 18በሁሉ ነገር አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና። 19መንፈስን አታዳፍኑ፤ 20ትንቢትን አትናቁ፤ 21ነገር ግን ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካሙንም አጥብቃችሁ ያዙ፤ 22ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።
23የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 24የሚጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።
25ወንድሞች ሆይ! ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ።
26ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።
27ይህ መልእክት ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ ዐደራ እላችኋለሁ።
28የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ