የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-51

1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-51 መቅካእኤ

ዳዊትም ሳኦልን፥ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ እኔ አገልጋይህ ሄጄ እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና ልጅ ነህ፥ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፥ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፥ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፥ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባርያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ ጌታ አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሲል ዳዊት ተናገረ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን!” አለው። ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ከናሐስ የተሠራ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበሰው። ዳዊትም ይህን ዓይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፥ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤ እርሱም ሳኦልን፥ “ያልተለማመድሁት ስለሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ያንን አወለቀው። ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፥ ወንጭፉን በእጁ ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም፥ ጋሻ ጃግሬውን ከፊት ከፊቱ በማስቀደም፥ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። እርሱም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው፥ ደም ግባት ያለው፥ መልከ መልካምና ልጅ ነበር፤ ስለዚህ በንቀት ዐይን ተመለከተው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። እርሱም ዳዊትን፥ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፥ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ ሁሉን በሚችል በሠራዊት ጌታ ስም እመጣብሃለሁ። ጌታ ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቆርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፤ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ እግዚአብሔር መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ ጌታ ያለ ሰይፍ ወይም ያለ ጦር እንደሚያድን ያውቃሉ፤ ሰልፉ የጌታ ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፥ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ በግምባሩም ምድር ላይ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።

Free Reading Plans and Devotionals related to 1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-51