1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 15
15
ሰባተኛው የአንጦዮኩስ ደብዳቤ እና የዶላ መያዝ
1የንጉሥ ዲሜጥሮስ ልጅ አንጥዮኩስ ከሜዲትሪንያን ባሕር አካባቢ ሆኖ ካህንና የአይሁዳውያን ሹም ለሆነው ለስምዖንና ለሕዝቡም ሁሉ ደብዳቤ ላከ፤ 2ደብደቤው የሚለው እንዲህ ነበር፥ “ንጉሥ አንጥዮኩስ ለሊቀ ካህናትና ለሕዝብ መሪ ስምዖንና ለአይሁድ ሕዝብም ሰላምታ ያቀርባል። 3ክፉ ሰዎች የአባቶቻችንን መንግሥት ስለያዙብኝ ይህን መንግሥት ልክ እንደ ቀድሞው ሆኖ እንዲመለስ ለማድረግ አስቤአለሁ፤ ስለዚህ ብዙ ወታደሮች ሰብስቤአለሁ፤ የጦር መርከቦችም አዘጋጅቻለሁ፤ 4ይህን ያደረግሁት ወደ እዚያ አገር ለመሻገር፥ አገራችንን የጠፉትንና የመንግሥቴ ከተሞች የደመሰሱትን ሰዎች ለመበቀል ነው። 5አሁንም ቢሆን ከእኔ በፊት የነበሩት ነገሥታት የተውልህን ግብርና ሌሎችንም የተውልህን ስጦታዎች ሁሉ እተውልሀለሁ። 6በአገርህ የሚያገለግለውን ገንዘብ አትመህ እንድታወጣ መብት ሰጥቼሃለሁ፤ 7ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ ነጻ ናቸው፤ የሠራሃቸው የጦር መሣሪያዎች ሁሉ፥ ያነጽኻቸው ምሽጐች ያንተ ሆነው ይቀራሉ፤ 8የአሁኑም ሆነ የወደፊቱ ለመንግሥት ግምጃ ቤት ገቢ መሆን የሚገባቸው ዕዳዎች ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ ለዘወትር ተትተውልሃል። 9መንግሥታችንን ከያዝን በኋላ ለአንተም ሆነ ለሕዝብህ፥ ለቤተ መቅደሱም ምስጋናችሁ ለመላው ዓለም ግልጽ የሚሆንበት ክብር ይሰጣችኋል”። 10በመቶ ሰባ አራት (139) ዓመተ ዓለም አንጥዮኩስ ወደ አባቶቹ አገር ሄደ፤ ወታደሮች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ከትሪፎን ጋር ጥቂት ሰዎች ብቻ ቀሩ። 11አንጥዮኩስ እየተከታተለ ትሪፎንን አባረረው፤ እርሱም በባሕር አጠገብ ወዳለችው ወደ ዶራ ሽሽቶ ሄደ፤ 12ምክንያቱም መካሪዎች እንደተመካከሩበትና ወታደሮችም እንደነገዱበት ስለተገነዘበ ነው። 13አንጥዮኩስ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ እግረኛ ጦረኞችና ከስምንት ሺህ ፈረሰኛ ጦረኞች ጋር ወደ ዶራ ሂዶ ሠፈረ። 14ከተማዋን ከበባት፤ መርከቦች በፊትዋ ተሰበሰቡ። ከተማዋም በምድርም፥ በባሕርም ስለተጠቃች ማንም መግባት ወይም መውጣት አይችልም ነበር። መልዕክተኞቹ ከሮም ወደ ይሁዳ ተመለሱ፤ ከሮም ጋር ያለው ግንኙነት ይፋ ተደረገ 15ኑመንዩስና ጓደኞቹ ለነገሥታትና ለሀገሮች የተጻፉትን ደብዳቤዎች ይዘው ከሮም ተመለሱ፤ የደብዳቤዎቹም ቃል እንዲህ የሚል ነው፤ 16“የሮማውያን ቆንሲል ሉስዮስ ለንጉሥ ጰጠሎማዎስ ሰላምታ ያቀርባል። 17ከሊቀ ካህናት ስምዖንና ከአይሁድ ሕዝብ የተላኩ መልእክተኞች የቀድሞውን ወዳጅነትና ቃል ኪዳን ለማደስ እንደ ወዳጆችና እንደ ጦር ጓደኞች ወደ እኛ መጡ፤ 18አንድ ሺህ ምናን የሚመዝን የወርቅ ጋሻ አመጡልን። 19ስለዚህ በክፉ ነገር እንዳይፈልጓቸው እነሱንም ሆነ ከተሞቻቸውን ወይም አገራቸውን እንዳይወጉ፥ እነርሱን ከሚይጓቸው ሰዎች ጋር እንዳይስማሙ ለነገሥታትና ለሀገሮች መጻፍ ወስነናል። 20ከእነርሱ የተላከልንንም ጋሻ ለመቀበል ወስነናል። 21ክፉ አደራጊዎች ከእነርሱ አገር ሸሽተው ወደ እናንተ ቢመጡ በሕጋቸው መሠረት እንዲቀጣቸው ለሊቀ ካህናት ስምዖን አሳልፋችሁ ስጧቸው”። 22ይህ ዓይነት ደብዳቤ ለዲሜጥርስና ለአጣሉስ፥ ለአርያራትና ለአርሳቂም ተጻፈ። 23እንዲሁም ለሀገሮች ሁሉ፥ ለሳምጳላሚ፥ ለጸሎስ፥ ለሚንጸስ፥ ለሊስዮን፥ ሊቃሪያ፥ ለሳሞስ፥ ለጹንፍልያ፥ ለሲቅያ፥ ለህሊቃርናስ፥ ለሮድስ፥ ለፋሊሌዳ፥ ለቆስ፥ ለሲደን፥ ለአራደን፥ ለጐሪቲና፥ ለቅኒዶስ፥ ለቆጱሮስ፥ ለቄራኔ፥ ተጻፈ። 24የደብዳቤዎቹ ግልባጭ ለሊቀ ካህናቱ ለስምዖን ተጽፎ ተሰጠው።
ሰባተኛው አንጥዮኩስ ዳራን ለመክበብ ተዘጋጀ፤ በዚህም የተነሣ ግጭት በመነሣቱ ለስምዖን ወቀሳ ላከበት።
25ንጉሥ አንጥዮኩስ ወታደሮች ወደ ዶራ ሳይቋርጡ እንዲጠጉ እያደረገና የጦር መዘውሮች እየሠራ በዶራ አጠገብ ሠፈረ፤ ትሪፎንን ዘግቶበት ስለ ነበር ማንም ሊገባ ወይም ሊወጣ አይችልም ነበር። 26እንዲዋጉለት ሁለት ሺህ ምርጥ ሰዎች ስምዖን ላከበት፤ እንዲሁም ብርና ወርቅ፤ ለትጥቅ የሚያስፈልጉ ብዙ እቃዎች ላከለት። 27አንጥዮኩስ ይህን መቀበል አልፈለገም፤ እንዲያውም ከዚህ ቀደም ከስምዖን ጋር ያደረገውን ውል ሁሉ አፈረሰ፤ ከዚህ ቀደም ከሰምዖን ጋር ያደረገውን ውል ሁሉ አፈረሰ፤ በስምዖንም ላይ ተለወጠበት። 28ከስምዖን ጋር እንዲነጋገር አጤኖበየስን ወደ ስምዖን ላከው፤ ንግግሩም እንዲህ የሚል ነበር፥ “የመንግሥቴ ከተሞች የሆኑትን ኢዮጶን፥ ጌዘርን፥ የኢየሩሳሌምን ምሽግ ይዛችኋል፤ 29ምድሮቻቸውን አጥፍታችኋል፤ በሀገሩ ላይ ብዙ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ የመንግሥቴን ብዙ ቦታቸውን ይዛችኋል፤ 30እንግዲህ አሁን የያዛችኋቸውን ከተሞች መልስ፤ ከይሁዳ ምድር ውጭ የሆኑትን የያዛችኋቸውን ቦታዎች ግብር ክፈል። 31አለበለዚያ በእነርሡ ፈንታ አምስት መቶ የብር መክሊት ሰጡ፤ ከዚህም በላይ ደግሞ ስላደረሳችሁት ጥፋትና ጉዳት፥ ስለከተሞች ግብር አምስት መቶ የብር መክሊት ተጨማሪ ስጡ፤ አይሆንም ካላችሁ መጥተን እንዋጋለን”። 32የንጉሡ ወዳጅ አጠኖብዮስ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ የስምዖንን ታላቅነት፥ በወርቅና በብር የተሠራውን ሣጥን፥ ብዙ ጌጣጌጥንም አየና በጣም አቀነቀ፤ የንጉሡንም ቃለ ለስምዖን ነገረው። 33ስምዖንም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኛ የያዝነው ጠላቶች ለጥቂት ጊዜ በግፍ የወሰድብንን የአባቶቻችንን ርስት ነው እንጂ የሌላውን ምድር ወይም የሌላውን ሰው ንብረት አይደለም። 34ምቹ ጊዜ አጋጥሞን ነው የአባቶቻችንን ርስት መመለስ የቻልነው። 35መልሱልን ስለምትላቸው ኢዮጴና ጌዘር እንደሆነ እነዚህ ከተሞች በሕዝቡና በሀገራችን ላይ ብዙ ክፉ ነገር ያደረጉ ናቸው፤ ለነዚህ አንድ መቶ መክሊት እንሰጣለን።” አጠናብዩስ ምንም ቃል አልተነፈሰም። 36በጣም ተቆጥቶ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ ይህን ነገርና ያየውን የስምዖንን ክብር ለንጉሡ ነገረው፤ ንጉሡም እጅግ በጣም ተቆጣ።
የጠረፍ አስተዳዳር ከንደብዮስ ይሁዳን ወጋ
37ትሪፎን በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ኦርቶሲያ ሸሽቶ ሄደ። 38ንጉሡ ከንደብዮስን የባሕሩ ጠረፍ አገር የጰራልያ የበላይ የጦር መሪ አድርጐ ሾመው፤ 39ሠፈሩን ከአይሁድ ፊት ለፊት እንዲያደርግ፤ ቄድሮንን እንደገነባ፤ መዝጊያዎችዋን እንዲያጠናክርና ሕዝቡንም እንዲወጋ አዘዘው፤ ንጉሡ ትሪፎንን ለመከታተል ገሠገሠ። 40ከንደክዮስ ወደ ያምንያ ሂዶ ሕዝቡን ማስቆጣትና ወደ ይሁዳ አገር መግባት፤ መማረክና ሰዎችን መጨረስ ጀመረ፤ 41ቴድሮንን እንደገና ገነባት አነጻት፤ ንጉሡ አዞት እንደነበረው መውጫ ለማግኘትና የይሁዳን አገር መንገዶች ለመሰለል ፈረሰኛና እግረኛ ወታደሮችን እዚያ አስቀመጠ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ