1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:1-37

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:1-37 መቅካእኤ

ሰሎሞን ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፥ ወርዱ አምሳ ክንድ፥ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፥ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። ቤቱ ከምሰ ሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ አምስት፥ በድምሩ አርባ አምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፥ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። ትይዩ የሆኑት የሕንጻው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው። በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለ አራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ። “ባለ ብዙ ምሰሶዎች” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ወርዱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በብዙ ምሰሶዎች የተደገፈና ጣራ የተሠራለት መመላለሻ ታዛም ነበረው። ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ ልጅ ለነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት። እነዚህ ሁሉ ሕንጻዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፤ ድንጋዮቹ በዚያም በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተጠርበውና ተከርክመው የመጡ ነበሩ። መሠረቱም የተሠራው በዚያው በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ ተዘጋጅተው በመጡ ታላላቅ ድንጋዮች ነበር፤ ከታላላቆቹም ድንጋዮች ውስጥ የአንዳንዱ ጥርብ ድንጋይ ርዝመት ሦስት ሦስት ሜትር ተኩል ሲሆን፥ የሌሎቹ ደግሞ አራት ሜትር ነበር። በእነዚህም ታላላቅ ድንጋዮች ላይ በልክ የተሠሩ ሌሎች ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ። የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፥ የጌታ ቤት ውስጣዊ አደባባይና ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ። ሰሎሞንም ሑራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አስጠራ። ሑራም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ ቀደም ብሎ የሞተው የሑራም አባትም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ የሑራም እናት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፤ ሑራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ ከንጉሥ ሰሎሞን በተደረገለት ጥሪ መሠረት መጥቶ የተመደበለትን የነሐስ ሥራ ሁሉ ሠራ። ሑራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ስምንት ሜትር፥ የዙሪያ ስፋታቸው አምስት ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ውስጡ ክፍት የሆነ አራት ጣት ውፍረት ካለው ነሐስ ሁለት ምሰሶዎችን ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት የነሐስ ጉልላቶችን ሠራ። በምሰሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፤ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት፥ ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ። ለየአንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ። በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጉልላቶች ቁመታቸው አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን የአሸንድዬ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር። እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጉልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ። ሑራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምሰሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፤ ከቤተ መቅደሱ መግቢያ በር በስተ ደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሰሶ ደግሞ ቦዔዝ ተባለ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የአሸንድዬ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ዓይነት ተፈጸመ። ሑራም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ጥልቀት፥ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የክብ ማእከል ርዝመት፤ ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ። የገንዳው አፍ ውጫዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ፥ ቅርጾች ነበሩት። ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ፤ ኰርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር። የገንዳው ጐኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የአሸንድዬ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር። ሑራም የእያንዳንዱ ርዝመት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ወርዱ አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ ዐሥር ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ። የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር። ልሙጥ በሆነው ነገርም ላይ በአንበሶች፥ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ፤ ከአንበሶቹ፥ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርጾች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጉንጉን የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኰራኲሮችና መንኰራኲሮቹ የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት ዐሥራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርጽ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም። የመንኰራኲሮቹም ቁመት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ መንኰራኲሮቹም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኰራኲሮችም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ መንኰራኲሮቹም የሠረገላ መንኰራኲሮችን ይመስሉ ነበር፤ ወስከምቶቻቸው፥ ቅትርቶቻቸውና ዐቃፊዎቻቸው ሁሉም ከነሐስ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። የእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘኖች በየግርጌአቸው ከእነርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት መደገፊያዎች ነበሩአቸው። በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርጽ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በእነዚሁ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፥ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል በተሠሩ ቅርጾች አጊጠው ነበር፤ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። እንግዲህ ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚህ ዓይነት ነበር። መጠናቸውና ቅርጻቸው እኩል ስለ ሆነ ሁሉም ተመሳሳይ ነበሩ።