የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 5

5
የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት መዘጋጀት
(2ዜ.መ. 2፥1-18)
1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ከዳዊት ጋር ወዳጅነቱን አጽንቶ ቆይቶ ነበር፤ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት እግር መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ መልእክተኞቹን ላከ። 2ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ላከ። 3“አባቴ ዳዊት በዙሪያው ከነበሩት የጠላት አገሮች ሠራዊት ጋር ሲዋጋ መኖሩን አንተ ራስህ ታውቀዋለህ፤ በጠላቶቹ ላይ ጌታ ድልን እስኪያጐናጽፈው ድረስ ለእግዚአብሔር ለጌታው ቤተ መቅደስ ለመሥራት አለመቻሉንም ታስታውሳለህ። 4አሁን ግን ጌታ እግዚአብሔር በሀገሬ ድንበር ዙሪያ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ምንም ዓይነት አደጋ የሚጥል ጠላት የለብኝም። 5#2ሳሙ. 7፥12፤13፤ 1ዜ.መ. 17፥11፤12።ጌታ ለአባቴ ለዳዊት ‘ከአንተ በኋላ የማነግሠው ልጅህ ለእኔ ቤተ መቅደስ ይሠራልኛል’ ሲል ተስፋ ሰጥቶት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ለጌታ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት እነሆ፥ አሁን ወስኛለሁ። 6ስለዚህ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የሚቆርጡ ሰዎችን ወደ ሊባኖስ ላክልኝ፤ የእኔም ሰዎች ከእነርሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ አደርጋለሁ፤ ለሰዎችህም አንተ የምትወስነውን ደመወዝ እከፍላለሁ፤ አንተ እንደምታውቀው የእኔ ሰዎች ስለ ዛፍ አቆራረጥ የአንተን ሰዎች ያኽል ዕውቀት የላቸውም።”
7ኪራምም የሰሎሞን መልእክት ሲደርሰው እጅግ ስለ ተደሰተ፥ “በእርሱ እግር ተተክቶ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ እንዲነግሥ ይህን የመሰለ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ ጌታ ይመስገን!” አለ። 8ከዚህ በኋላ ኪራም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለሰሎሞን ላከ፦ “ያስተላለፍከው መልእክት ደርሶኛል፤ አንተ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባውን ግንድ አዘጋጅቼ አቀርብልሃለሁ። 9የእኔ ሰዎችም ግንዶቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዳሉ፤ አንድነት ጠፍረው አስረውም አንተ ወደምትመርጠው ጠረፍ ተንሳፍፈው እንዲደርሱ ያደርጋሉ፤ በዚያም የእኔ ሰዎች ማሰሪያውን ፈተው ለአንተ ሰዎች ያስረክቡአቸዋል፤ አንተም በበኩልህ በቤተ መንግሥቴ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምግብ በመላክ ፍላጎቴን ታረካለህ።”
10በዚህ ዓይነት ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖስን ዛፍና የዝግባ ግንድ ሁሉ አቀረበለት። 11ሰሎሞንም በበኩሉ በኪራም ቤተ መንግሥት ውስጥ ላሉት ሰዎች ቀለብ የሚሆን ሁለት ሺህ ቶን ስንዴና አራት መቶ ሺህ ሊትር ንጹሕ የወይራ ዘይት በየዓመቱ ይሰጥ ነበር።
12ጌታ አስቀድሞ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞን መካከል ሰላም ስለ ነበረ ሁለቱም የጋራ ስምምነት ውል አደረጉ።
13ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል ሠላሳ ሺህ የግዳጅ ሠራተኞችን መለመለ። 14#1ነገ. 12፥18።በእነርሱ ላይ አዶኒራም የተባለውን ሰው ኀላፊ አድርጎ ሾመ፤ ሠራተኞቹንም ዐሥር ዐሥር ሺህ አድርጎ በሦስት ቡድን በመክፈል እያንዳንዱ ቡድን ተራ ገብቶ አንድ ወር በሊባኖስ እንዲሠራ፥ ሁለት ወር ደግሞ በቤቱ እንዲያርፍ ወሰነ። 15ንጉሥ ሰሎሞን በኮረብታማው አገር ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ፥ የተፈለጠውን ድንጋይ ተሸክመው የሚያመጡ ሰባ ሺህ ሰዎችን መደበ። 16የእነዚህ ሠራተኞች የበላይ ሆነው ሥራውን የሚቆጣጠሩ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ሰዎችን አዘጋጀ። 17በዚህ ዓይነት ሠራተኞቹ በንጉሥ ሰሎሞን ትእዛዝ ለቤተ መቅደሱ መሠረት የሚሆኑ ታላላቅ ድንጋዮችን ፈለጡ። 18የሰሎሞንና የኪራም ጥበበኞች ሠራተኞችና እንዲሁም የቢብሎስ ሰዎች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ አዘጋጁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ