1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 17
17
ኤልያስ የድርቅ ጊዜ ስለ መምጣቱ ተናገረ
1 #
ያዕ. 5፥17። በገለዓድ የምትገኘው የቱቢ ተወላጅ የሆነውና ኤልያስ ተብሎ የሚጠራው ነቢይ፤ ንጉሥ አክዓብን “በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር በሚቀጥሉት ዓመቶች በምድር ላይ ጠል ወይም ዝናብ እንደማይኖር እኔ በማገለግለው በእስራኤል አምላክ፥ በሕያው ጌታ ስም እነግርሃለሁ” አለው።
2ከዚህ በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤልያስ መጣ። 3“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ እዚያም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ከሪት ተብሎ በሚጠራው ሸለቆ ተሸሸግ። 4የምትጠጣውንም ውሃ ከዚያው ወንዝ ታገኛለህ፤ ቁራዎችም ምግብ እንዲያመጡልህ አዝዣለሁ።”
5ኤልያስም ጌታ ባዘዘው መሠረት ሄዶ በከሪት ሸለቆ ተቀመጠ። 6ከወንዙም ውሃ ጠጣ፤ ቁራዎችም ዘወትር ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር። 7ዝናብ ጠፍቶ ድርቅ ከመሆኑ የተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ወንዝ ደረቀ።
ኤልያስና በስራጵታ ትኖር የነበረች መበለት
8ከዚህ በኋላ ጌታ ኤልያስን እንዲህ አለው፤ 9#ሉቃ. 4፥25፤26።“እንግዲህ አሁን ከዚህ ተነሥተህ ሂድና በሲዶና በምትገኘው በስራጵታ ከተማ ተቀመጥ፤ እነሆ በዚያ የምትኖር አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ” አለው። 10ስለዚህ ኤልያስ ወደ ሰራጵታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም ቅጽር በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባሏ የሞተባት ሴት እንጨት ስትለቅም አይቶ “እባክሽ የምጠጣው ውሃ አምጪልኝ” አላት። 11ውሃም ልታመጣለት በመሄድ ላይ ሳለች ወዲያውኑ ጠርቶ “እባክሽ በተጨማሪ ትንሽ እንጀራ አምጪልኝ” አላት።
12እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ምንም እንጀራ እንደሌለኝ በአምላክህ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ፤ በዱቄት ዕቃዬ ውስጥ ካለችው ከአንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮዬ ውስጥ ካለችው ከጥቂት የወይራ ዘይት በቀር ምንም የለኝም፤ ወደዚህ የመጣሁት ትንሽ እንጨት ለቃቅሜ ወደ ቤቴ በመመለስ ይህችኑ ያለችኝን ትንሽ ዱቄት ለልጄና ለእኔ ለመጋገር ነው፤ ይህችም የመጨረሻ ምግባችን ናት፤ ከዚያም በኋላ በራብ ከመሞት አንተርፍም።”
13ኤልያስም እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትጨነቂ! ሄደሽ ምግብሽን አዘጋጂ፤ አስቀድመሽ ግን ከዚያችው ካለችሽ ዱቄት ለእኔ ትንሽ እንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ የቀረውንም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪው፤ 14የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ‘ጌታ ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮው ዘይት አያልቅም።’”
15እርሷም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህም ዓይነት እርሷ፥ ቤተሰብዋና ኤልያስም ለብዙ ቀን የሚሆን በቂ ምግብ አገኙ። 16ጌታ በኤልያስ አማካይነት በሰጠው ተስፋ መሠረት ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፥ ዘይቱም ከማሰሮው አላለቀም።
17ከጥቂት ጊዜም በኋላ የዚያች ባሏ የሞተባት ሴት ልጅ ታመመ፤ ሕመሙም እየባሰበት ስለ ሄደ በመጨረሻ ሞተ። 18እርሷም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ስለምን ይህን አደረግህብኝ? ወደዚህ የመጣኸው ኃጢአቴን አስታውሰህ ልጄ እንዲሞትብኝ ለማድረግ ነውን?” ስትል ጠየቀችው።
19ኤልያስም “ልጅሽን ወደ እኔ አምጪው” አላት። ልጁንም ከዕቅፍዋ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት አውጥቶ በአልጋው ላይ አጋደመው። 20ከዚህ በኋላ ኤልያስ ድምፁን ከፍ በማድረግ “ጌታ አምላኬ ሆይ! ስለምን በዚህች ባሏ በሞተባት ሴት ላይ ይህን የመሰለ አሠቃቂ ነገር አደረግህ? እርሷ እኔን በማስተናገድ ታላቅ ቸርነት አድርጋልኛለች፤ ታዲያ አንተ ስለምን ልጇ እንዲሞት አደረግህ?” ሲል ጸለየ። 21#2ነገ. 4፥34፤35።ከዚህ በኋላ ኤልያስ በልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርሮ “ጌታ አምላኬ ሆይ! እባክህ ይህን ልጅ ከሞት አስነሣው!” ሲል ጸለየ። 22ጌታም የኤልያስን ጸሎት ሰማ፤ የልጁም እስትንፋስ እንደገና ተመልሶለት ዳነ።
23ኤልያስ ልጁን ከሰገነት ወደ ምድር ቤት አውርዶ ለእናቱ በመስጠት “ተመልከቺ፤ እነሆ ልጅሽ ከሞት ወደ ሕይወት ተመልሶአል!” አላት።
24ሴትዮዋም “እነሆ አንተ የእግዚአብሔር ሰው መሆንህንና በአፍህ ያለው የጌታ ቃል እውነት እንደሆነ አሁን አወቅሁ!” ስትል መለሰችለት።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 17: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ