1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9:1-12

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9:1-12 መቅካእኤ

እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና፥ ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ። ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ አማኝ ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማን ነው? ይህን የምናገረው በሰው አስተሳሰብ ብቻ ነውን? ሕግስ እንዲህ ይል የለምን? “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፎአል። እግዚአብሔር ይህን ያለው ስለ በሬዎች በማሰብ ነውን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? በእርግጥ ስለ እኛ ተጽፎአል፥ ይኸውም የሚያርስ በተስፋ እንዲያርስ፥ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው ነው። እኛ መንፈሳዊን ነገር ከዘራንላችሁ፥ የእናንተን የሥጋዊን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን የመካፈል መብት ያላቸው ከሆነ፥ እኛማ ይልቁን አይኖረንም? በዚህ መብት ግን አልተጠቀምንም፥ ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል በምንም እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ።