1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9

9
1እስራኤልም ሁሉ በየትውልዳቸው ተቈጠሩ፤ እነሆም፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጻፉ። ይሁዳም ስለ ኃጢአታቸው ወደ ባቢሎን ተማረኩ። 2#ዕዝ. 2፥70፤ 7፥7፤ ነህ. 11፥3።በአውራጃዎቻቸውና በከተሞቻቸው መጀመሪያ የተቀመጡ እስራኤልና ካህናት ሌዋውያንም የቤተ መቅደሱም አገልጋዮች ነበሩ።
ከምርኮ በኋላ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች
3ከይሁዳ ልጆችና ከብንያም ልጆች ከኤፍሬምና ከምናሴ ልጆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 4ከይሁዳ ልጅ ከፋሬስ ልጆች የባኒ ልጅ የአምሪ ልጅ የዖምሪ ልጅ የዓሚሁድ ልጅ ዑታይ ደግሞ በዚያ ተቀመጠ። 5ከሴሎናውያንም በኩሩ ዓሣያና ልጆቹ በዚያ ተቀመጡ። 6ከዛራም ልጆች ይዑኤልና ወንድሞቻቸው፥ ስድስት መቶ ዘጠና ነበሩ። 7ከብንያምም ልጆች የሐስኑአ ልጅ የሆዳይዋ ልጅ የሜሱላም ልጅ ሰሉ ነበር፤ 8የይሮሐም ልጅ ብኔያ፤ የሚክሪ ልጅ የኦዚ ልጅ ኤላ ነበር፤ የይብንያ ልጅ የራጉኤል ልጅ የሰፋጥያስ ልጅ ሜሱላም ነበር፤ 9በየትውልዳቸውም ወንድሞቻቸው ዘጠኝ መቶ ኀምሳ ስድስት ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ።
የካህናት ወገን
10ከካህናቱም ዮዳኤ፥ ዮአሪብ፥ ያኪን ነበሩ፤ 11የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ የመራዮት ልጅ የሳዶቅ ልጅ የሜሱላም ልጅ የኬልቅያስ ልጅ ዓዛርያስ ነበር፤ 12የመልክያ ልጅ የጳስኮር ልጅ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ ነበር፤ የኢሜር ልጅ የምሺላሚት ልጅ የሜሱላም ልጅ የየሕዜራ ልጅ የዓዲኤል ልጅ መዕሣይ ነበር፤ 13የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ወንድሞቻቸው ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ነበሩ፤ ለእግዚአብሔር ቤት ለሚከናወነው የአገልግሎት ሥራ እጅግ ብቃት ያላቸው ሰዎች ነበሩ።
የሌዋውያን ወገን
14ከሌዋውያንም የሜራሪ ልጆች የአሳብያ ልጅ የዓዝሪቃም ልጅ የአሱብ ልጅ ሸማያ ነበር፤ 15በቅበቃር፥ ኤሬስ፥ ጋላል፥ የአሳፍ ልጅ የዝክሪ ልጅ የሚካ ልጅ መታንያ ነበር፤ 16የኤዶታም ልጅ የጋላል ልጅ የሰሙስ ልጅ አብድያ ነበር፤ በነጦፋውያንም መንደሮች የተቀመጠው የሕልቃና ልጅ የአሳ ልጅ በራክያ ነበር።
17በርም ጠባቂዎች ሰሎም፥ ዓቁብ፥ ጤልሞን፥ አሒማን፥ ወንድሞቻቸውም ነበሩ፤ ሰሎምም አለቃ ነበረ። 18እስከ ዛሬም ድረስ በንጉሥ በር በምሥራቅ በኩል ሰፍረዋል፤ ለሌዊ ልጆች ሰፈር በርም ጠባቂዎች ነበሩ። 19የቆሬም ልጅ የአብያሳፍ ልጅ የቆሬ ልጅ ሰሎም ከአባቱም ቤት የነበሩ ወንድሞቹ ቆሬያውያን በማገልገል ሥራ ላይ ነበሩ፥ አባቶቻቸውም የጌታን ሰፈር መግቢያ ይጠብቁ እንደ ነበር እንዲሁ የድንኳኑን የመግቢያ ደጅ ይጠብቁ ነበር።። 20አስቀድሞም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ አለቃቸው ነበረ፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነበረ። 21የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ የመገናኛው ድንኳን ደጅ ጠባቂ ነበረ። 22የመግቢያው ደጅ ጠባቂዎች እንዲሆኑ የተመረጡ እነዚህ ሁሉ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል በሥራቸው ያቆሙአቸው እነዚህ በመንደሮቻቸው በየትውልዳቸው ተቈጠሩ። 23እነርሱና ልጆቻቸውም በጌታ ቤት በድንኳኑ ደጆች ላይ ዘበኞች ነበሩ። 24በአራቱ ማዕዘኖች፥ በምሥራቅ፥ በምዕራብ፥ በሰሜን፥ በደቡብ፥ ጠባቂዎች ነበሩ። 25በመንደሮቸቻቸውም የነበሩ ወንድሞቻቸው በየሰባትም ቀን ከእነርሱ ጋር አብረው ለመሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይመጡ ነበር። 26ከሌዋውያንም የነበሩ አራቱ የጠባቂዎች አለቆች በሥራቸው ታማኞች ነበሩ፤ በጌታም ቤት ባሉ ጓዳዎችና ቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው ነበር። 27የእግዚአብሔርንም ቤት የሚጠብቁ፥ ጥዋት ጥዋትም ደጆቹን የሚከፍቱ እነርሱ ነበሩና በዚያ ያድሩ ነበር።
28ዕቃውም በቍጥር፥ ይገባና ይወጣ ነበርና ከእነዚህ እያንዳንዱ በመገልገያው ዕቃ ላይ ሹሞች ነበሩ። 29ከእነርሱም አንዳንዶቹ በመቅደሱ ዕቃ ሁሉ በመልካሙም ዱቄት፥ በወይን ጠጁም፥ በዘይቱም፥ በዕጣኑም፥ በሽቶውም ላይ ሹሞች ነበሩ። 30ከካህናቱም ልጆች አንዳንዶቹ የሽቶውን ቅባት ይቀምሙ ነበር። 31የቆሬያዊውም የሰሎም በኩር ሌዋዊው ማቲትያ በምጣድ በሚጋገረው ኅብስት ላይ ሹም ነበረ። 32ከወንድሞቻቸውም ከቀዓታውያን አንዳንዶቹን በየሰንበቱ የተቀደሰውን ኅብስት እንዲያዘጋጁ ሹሞች ነበሩ።
33ከሌዋውያንም ወገን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች የነበሩ መዘምራን እነዚህ ናቸው፤ ሥራቸውም ሌሊትና ቀን ነበረና ያለ ሌላ ሥራ በየእልፍኛቸው ይቀመጡ ነበር። 34እነዚህ ከሌዋውያን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች በየትውልዳቸውም አለቆች ነበሩ። እነዚህም በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ነበር።
የንጉሥ ሳኦል ቤተሰብ
35የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው በገባዖን የተቀመጠው የገባዖን አባት ይዒኤል፥ 36የበኩር ልጁም ዓብዶን፥ ከዚያም በኋላ ዱር፥ ቂስ፥ በኣል፥ ኔር፥ ናዳብ፥ 37ጌዶር፥ አሒዮ፥ ዛኩር፥ ሚቅሎት ነበሩ። 38ሚቅሎትም ሳምአን ወለደ፤ እነርሱ ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ይቀመጡ ነበር። 39ኔርም ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሜልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስባኣልን ወለደ። 40የዮናታንም ልጅ መሪበ-ኣል ነበረ፤ መሪበ-ኣልም ሚካን ወለደ። 41የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሪዓ፥ አካዝ ነበሩ። 42አካዝም የዕራን ወለደ፤ የዕራም ዓሌሜትን፥ ዕዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ሞጻን ወለደ። 43ሞጻም ቢንዓን ወለደ፥ ልጁም ረፋያ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል ነበሩ፤ 44ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ዓዝሪቃም፥ ቦክሩ፥ እስማኤል፥ ሸዓርያ፥ አብድዩ፥ ሐናን፤ እነዚህ የኤሴል ልጆች ነበሩ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ