1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19

19
አሞናውያንና ሶርያውያን መሸነፋቸው
1ከዚህም በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2ዳዊትም፦ “አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባርያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። 3የአሞን ልጆች ሹማምንት ግን ሐኖንን እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባርያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን?” 4ሐኖንም የዳዊትን ባርያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው፤ 5እነርሱም ወደመጡበት ተመለሱ። ዳዊትም በሰዎቹ ላይ የተደረገውን በነገረሩት ጊዜ ሰዎቹ እጅግ ስላፈሩ እንዲቀበሏቸው መልእክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፦ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ” አለ።
6የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራም-መዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመቅጠር አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ። 7ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሠራዊት ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ውግያ መጡ። 8ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። 9የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ለውግያ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ ነበሩ።
10ኢዮአብም ውግያው በፊትና በኋላ እንደሚደረግ ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው። 11የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፤ እነርሱም በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ። 12እርሱም እንዲህ አለ፦ “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። 13አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ ጌታም ደስ ያሰኘውን ያድርግ።” 14ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለውግያ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። 15የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
16ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ። 17ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ ለውግያ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። 19የአድርአዛርም ባርያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ለመርዳት እንቢ አሉ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ