1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 13
13
ታቦቱ ከቂርያት-ይዓሪም መመለሱ
1ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከሹማምንቱም ሁሉ ጋር ተማከረ። 2ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “መልካም መስሎ ቢታያችሁ፥ የጌታም የአምላካችን ፈቃድ ቢሆን፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰማሪያዎቻቸውም ለተቀመጡት ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ እንዲሰበሰቡ እንላክባቸው፤ 3በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ።” 4ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ፦ “እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። 5#1ሳሙ. 7፥1፤2።የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያት-ይዓሪም ለማምጣት ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሆር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። 6#ዘፀ. 25፥22።ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የጌታን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያት-ይዓሪም ወደተባለች ወደ በኣላ ሄዱ። 7የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር። 8ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በዝማሬና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጸልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ያሸበሽቡ ነበር።
9ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። 10የጌታም ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። 11ጌታም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ-ስብራት ብሎ ጠራው። 12#2መቃ. 7፥19።በዚያም ቀን ዳዊት፦ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ?” ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ።
13ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢ-ዳራ ቤት ወሰደው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም። 14#1ዜ.መ. 26፥4፤5።የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢ-ዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ ጌታም የአቢ-ዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 13: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ