የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 14

14
ኢየሩሳሌምና የአሕዛብ መንግሥታት
1የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ደርሶአል፤ በዚያን ጊዜ ዐይናችሁ እያየ በዝባዦች ከእናንተ የወሰዱትን ይካፈሉታል። 2ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ እግዚአብሔር ሕዝቦችን ሰብስቦ ይመጣል፤ ከተማይቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ከሕዝቡም እኩሌታው ተማርኮ ይሄዳል፤ የቀሩት ግን ከከተማይቱ አይወጡም። 3ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ ሕዝቦችን ለመውጋት ይነሣል። 4በዚያን ቀን እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማል፤ የደብረ ዘይት ተራራም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሰፊ ሸለቆ በሁለት ይከፈላል፤ ስለዚህም የተራራው እኩሌታ ወደ ሰሜን እኩሌታውም ወደ ደቡብ ፈቀቅ ይላል። 5እናንተም ተራራውን በሁለት ከፍሎ እስከ አጻል በደረሰው በዚህ ሸለቆ ውስጥ አልፋችሁ ታመልጣላችሁ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ምድር በተናወጠች ጊዜ የቀድሞ አባቶቻችሁ በሸሹት ዐይነት ትሸሻላችሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬም ቅዱሳኑን አስከትሎ ይመጣል።
6በዚያን ዘመን ውርጭና ዐመዳይ ጨለማም ከቶ አይኖርም፤ 7በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ አንድ ተከታታይ ቀን ይመጣል፤ በምሽት ጊዜ ብርሃን ስለሚሆን ቀንም ሌሊትም የለም።
8በዚያን ቀን ከኢየሩሳሌም የሕይወት ውሃ ይፈልቃል፤ ከእርሱም እኩሌታው በምሥራቅ በኩል ወደ ሙት ባሕር፥ እኩሌታው በምዕራብ በኩል ወደ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይፈስሳል፤ በበጋም ሆነ በክረምት ዓመቱን ሙሉ ሲፈስ ይኖራል። #ሕዝ. 47፥1፤ ዮሐ. 7፥38፤ ራዕ. 22፥1። 9በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይነግሣል፤ ሰዎችም አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያምናሉ፤ የእርሱንም ስም ብቻ ይጠራሉ።
10በሰሜን ከጌባዕ አንሥቶ ኢየሩሳሌምን በደቡብ በኩል አልፎ እስከ ሪሞን ድረስ ያለው አውራጃ ደልዳላ ይሆናል፤ ኢየሩሳሌም በዙሪያዋ ካለው ምድር በላይ ከፍ ትላለች፤ ከተማይቱም ከብንያም በር አንሥቶ በቀድሞው በር አቅጣጫ እስከ ማእዘን በር እንዲሁም ከሐናንኤል ግንብ አንሥቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ ወይን መጭመቂያው ድረስ ከፍ በማለት ጸንታ ትኖራለች። 11ኢየሩሳሌም የሕዝብ መኖሪያ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት አይደርስባትም፤ ሕዝብዋም ያለ ስጋት በሰላም ይኖራል። #ራዕ. 22፥3።
12ኢየሩሳሌምን ለመውጋት በሚነሣሡ ሕዝቦች ላይ እግዚአብሔር ቀሣፊ በሽታ ያመጣባቸዋል፤ በሕይወት እያሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይናቸው በዐይነስባቸው ውስጥ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል።
13በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ሁከትና ፍርሀት ስለሚለቅባቸው እያንዳንዱ ሰው በአጠገቡ ያለውን ሌላ ሰው ይዞ አደጋ ይጥልበታል። 14የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ለመከላከል ይዋጋሉ፤ በዙሪያዋም ያሉትን መንግሥታት ሀብት ሁሉ ማርከው ይወስዳሉ፤ ከሚወስዱትም ምርኮ ወርቅ፥ ብርና የልብስ ዐይነት እጅግ ብዙ ይሆናል።
15ያንን የሚመስል ቀሣፊ በሽታ በጠላት ሰፈር ባሉ እንስሶች በፈረሶች፥ በበቅሎዎች፥ በግመሎችና በአህዮች ሁሉ ላይ ይመጣል።
16ከዚያም በኋላ ኢየሩሳሌምን ከወጉአት መንግሥታት መካከል ከጥፋት የተረፉት ለንጉሡ ለሠራዊት አምላክ ሊሰግዱለትና የዳስ በዓልንም ለማክበር በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣሉ። #ዘሌ. 23፥39-43። 17ለንጉሡ ለሠራዊት አምላክ የማይሰግዱለት ሕዝቦች ቢኖሩ በምድራቸው ዝናብ አይዘንብላቸውም። 18ግብጻውያንም በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ ባይፈልጉ፥ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተን የዳስ በዓል አናከብርም” በሚሉ መንግሥታት ላይ የሚደርሰው ቀሣፊ በሽታ ይመጣባቸዋል። 19ግብጻውያንም ሆኑ ሌሎች መንግሥታት “የዳስ በዓል አናከብርም” ቢሉ የሚደርስባቸው ቅጣት ይህ ነው።
20በዚያን ጊዜ በፈረሶች አንገት ላይ በሚንጠለጠል ቃጭል ሁሉ ላይ “ለእግዚአብሔር የተለየ” የሚል የጽሕፈት ምልክት ይቀረጽበታል፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለው የማብሰያ ማሰሮ በመሠዊያው ላይ እንደሚገኘው ሳሕን የተቀደሰ ይሆናል። 21በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር የሚገኘው ማሰሮ ሁሉ ለሠራዊት አምላክ የተለየ ይሆናል፤ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች ሁሉ በማሰሮዎቹ ጥቂቱን የመሥዋዕቱን ሥጋ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ የሚነግድ ማንም ሰው አይኖርም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ