እስቲ ደግሞ ልጠይቅ፦ እግዚአብሔር የራሱን ሕዝብ ጥሎአልን? ከቶ አልጣለውም! እኔም ራሴ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከአብርሃም ዘር የሆንኩ የብንያም ነገድ ነኝ። እግዚአብሔር አስቀድሞ የመረጠውን ሕዝብ አልጣለውም፤ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ኤልያስ ምን እንዳለ አታስታውሱምን? ደግሞስ ኤልያስ የእስራኤልን ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ምን ብሎ እንደ ከሰሰ አታውቁምን? በዚያን ጊዜ ኤልያስ “ጌታ ሆይ! ነቢያትህን ገደሉ፤ መሠዊያዎችህን አፈረሱ፤ እኔ ብቻ ቀረሁ፤ እኔንም ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ብሎ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ምን ብሎ መለሰለት? “ባዓል ለተባለው ጣዖት ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ” ብሎታል። በአሁኑም ዘመን ቢሆን፥ በጸጋ ተመርጠው የቀሩ ጥቂት እስራኤላውያን አሉ። ምርጫው በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም ማለት ነው፤ በሥራ ከሆነማ፥ ጸጋ ዋጋቢስ በሆነ ነበር። ታዲያ፥ ውጤቱ ምን ሆነ? እስራኤላውያን የፈለጉትን አላገኙም፤ የተመረጡት ግን የፈለጉትን አገኙ፤ የቀሩት ልባቸውን አደነደኑ። ይህም “እግዚአብሔር ልቡናቸውን አደነዘዘ፤ ስለዚህ እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው አያዩም፤ በጆሮአቸውም አይሰሙም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ዳዊትም፦ “ማእዳቸው የሚይዝ ወጥመድ፥ የሚጥል ጒድጓድ ሆኖ ያሠቃያቸው! ያደረጉት ክፋት በራሳቸው ላይ ይድረስ! ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤ ወገባቸውም በችግር ሁልጊዜ ይጒበጥ” ብሎአል። እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው። የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር! አሁን እንግዲህ የምናገረው ለእናንተ ለአሕዛብ ነው፤ የአሕዛብም ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን በአገልግሎቴ ክብር ይሰማኛል፤ ይህንንም ማድረጌ የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑትን አይሁድ ለማስቀናት ነው፤ በዚህም ሁኔታ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዶቹን ለማዳን እችል ይሆናል በማለት ነው። እግዚአብሔር እነርሱን በጣላቸው ጊዜ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀበላቸው ጊዜ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይህማ ከሞት እንደ መነሣት ያኽል ነው! ከአንድ ዐይነት ሊጥ የመጀመሪያው ክፍል የተቀደሰ ከሆነ ሊጡ በሙሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ሥሩ የተቀደሰ ከሆነ ቅርንጫፎቹም የተቀደሱ ይሆናሉ። እንደ ጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑ አይሁድ ተቈርጠው ቢወድቁና እናንተ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆናችሁ አሕዛብ በቦታቸው ተተክታችሁ የእነርሱን ሀብትና በረከት ተካፋዮች ብትሆኑ፥ እናንተ አሕዛብ እንደ ቅርንጫፍ ተቈርጠው በወደቁት አይሁድ ላይ አትታበዩ፤ ብትታበዩ ግን እናንተ ቅርንጫፎች ብቻ በመሆናችሁ ሥሩ እናንተን ይሸከማችኋል እንጂ እናንተ ሥሩን የማትሸከሙ መሆናችሁን አስታውሱ። ነገር ግን “ቅርንጫፎች ተሰብረው የወደቁት እኔ በቦታቸው እንድተካ ነው” ትሉ ይሆናል። አባባላችሁስ ልክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ተቈርጠው የወደቁት ባለማመናቸው ሲሆን እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁት በማመናችሁ ነው፤ ታዲያ፥ መፍራት እንጂ መታበይ አይገባችሁም። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት አይሁድ ካልራራላቸው ለእናንተም አይራራላችሁም።
ወደ ሮም ሰዎች 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮም ሰዎች 11:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች