የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 12:4-12

የዮሐንስ ራእይ 12:4-12 አማ05

በጅራቱ የኮከቦችን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ልጅዋን ለመዋጥ አስቦ ዘንዶው ልትወልድ ወደተቃረበችው ሴት ከፊት ለፊትዋ ቆመ፤ ሴቲቱም ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋ ግን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተወሰደ፤ ሴቲቱም ወደ በረሓ ሸሽታ ሄደች፤ እዚያ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን በእንክብካቤ ተይዛ የምትጠበቅበትን ስፍራ እግዚአብሔር አዘጋጅቶላት ነበር። በሰማይ ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና የእርሱ መላእክት ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፥ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጉ። ከእርሱ መላእክት ጋር ተዋጉ፤ ነገር ግን ዘንዶውና የእርሱ መላእክት ተሸነፉ፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ታላቁም ዘንዶ ወደታች ተጣለ፤ እርሱ መላውን ዓለም የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው። እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ የእርሱም መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ተጣሉ። ከዚህ በኋላ አንድ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “እነሆ አዳኝነት፥ ኀይል፥ መንግሥትም የአምላካችን ሆኖአል! ሥልጣንም የመሲሑ ሆኖአል! ወንድሞቻችንን በአምላካችን ፊት ቀንና ሌሊት ሲያሳጣቸው የነበረ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአል፤ እነርሱ በበጉ ደምና በተናገሩት የምስክርነት ቃል ድል ነሥተውታል፤ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፤ ስለዚህ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ጥቂት ጊዜ ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ ዲያብሎስ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና ምድርና ባሕር ወዮላችሁ!”