የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 12

12
ሴቲቱና ዘንዶው
1ከዚህ በኋላ ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የለበሰች፥ ጨረቃን ከእግርዋ በታች ያደረገች፥ ዐሥራ ሁለት ኮከቦችን እንደ አክሊል በራስዋ ላይ የደፋች፥ አንዲት ሴት ታየች። 2እርስዋም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድም ምጥ ይዞአት ተጨንቃ ትጮኽ ነበር፤
3እንዲሁም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት ትልቅ ቀይ ዘንዶ ታየ፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ደፍቶ ነበር፤ #ዳን. 7፥7። 4በጅራቱ የኮከቦችን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ልጅዋን ለመዋጥ አስቦ ዘንዶው ልትወልድ ወደተቃረበችው ሴት ከፊት ለፊትዋ ቆመ፤ #ዳን. 8፥10። 5ሴቲቱም ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋ ግን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተወሰደ፤ #ኢሳ. 66፥7፤ መዝ. 2፥9። 6ሴቲቱም ወደ በረሓ ሸሽታ ሄደች፤ እዚያ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን በእንክብካቤ ተይዛ የምትጠበቅበትን ስፍራ እግዚአብሔር አዘጋጅቶላት ነበር።
7በሰማይ ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና የእርሱ መላእክት ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፥ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጉ። ከእርሱ መላእክት ጋር ተዋጉ፤ #ዳን. 10፥13፤21፤ 12፥1፤ ይሁዳ 9። 8ነገር ግን ዘንዶውና የእርሱ መላእክት ተሸነፉ፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። 9ታላቁም ዘንዶ ወደታች ተጣለ፤ እርሱ መላውን ዓለም የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው። እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ የእርሱም መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ተጣሉ። #ዘፍ. 3፥1፤ ሉቃ. 10፥18።
10ከዚህ በኋላ አንድ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “እነሆ አዳኝነት፥ ኀይል፥ መንግሥትም የአምላካችን ሆኖአል! ሥልጣንም የመሲሑ ሆኖአል! ወንድሞቻችንን በአምላካችን ፊት ቀንና ሌሊት ሲያሳጣቸው የነበረ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአል፤ #ኢዮብ 1፥9-11፤ ዘካ. 3፥1። 11እነርሱ በበጉ ደምና በተናገሩት የምስክርነት ቃል ድል ነሥተውታል፤ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፤ 12ስለዚህ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ጥቂት ጊዜ ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ ዲያብሎስ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና ምድርና ባሕር ወዮላችሁ!”
13ዘንዶው ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት፤ 14ሴቲቱ በበረሓ ወደ ተዘጋጀላት ስፍራ በርራ እንድትሄድ የታላቅ ንስር ክንፎች የሚመስሉ ሁለት ክንፎች ተሰጡአት፤ እዚያም ከእባቡ ፊት ርቃ ሦስት ዓመት ተኩል በእንክብካቤ ተይዛ ትጠበቅ ነበር። #ዳን. 7፥25፤ 12፥7። 15ሴቲቱ በጐርፍ እንድትወሰድ ብሎ እባቡ የወንዝ ውሃ የሚያኽል ውሃ ከአፉ ተፍቶ በስተኋላዋ አፈሰሰ። 16ነገር ግን ምድር ሴቲቱን ረዳቻት፤ አፍዋንም ከፈተችና ዘንዶው ከአፉ ተፍቶ ያፈሰሰውን ውሃ መጠጠች። 17ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ ከቀሩት የእርስዋ ዘር ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስ በታማኝነት የሚመሰክሩ ናቸው። 18ዘንዶውም በባሕሩ ዳር አሸዋ ላይ ቆመ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ