የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 88

88
የእግዚአብሔርን ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ልመና
1አዳኜ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ!
ትረዳኝ ዘንድ በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፤
ሌሊቱንም በአንተ ፊት አለቅሳለሁ።
2እባክህ ጸሎቴን ስማ!
ጩኸቴንም አድምጥ!
3ብዙ መከራ ስለ ደረሰብኝ
ለመሞት ተቃርቤአለሁ።
4ሞተው ወደ መቃብር ከሚወርዱት ሰዎች ጋር ተቈጥሬአለሁ፤
ምንም ረዳት እንደሌለው ሰው ሆኜአለሁ።
5በሙታን መካከል ፈጽሞ እንደ ተተዉ፥
ተገድለው በመቃብር እንደ ተጋደሙ፥
ከእንግዲህ ፈጽሞ እንደማታስታውሳቸውና
የአንተ እንክብካቤ ከእነርሱ እንደ ተቋረጠ ሰዎች መስዬአለሁ።
6አንተ ወደ መቃብር አዘቅት
ወደ ጨለመውና ጥልቅ ወደ ሆነው ጒድጓድ አወረድከኝ።
7ቊጣህ እጅግ ከብዶኛል፤
የቊጣህም ማዕበል አጥለቅልቆኛል።
8ወዳጆቼ ሁሉ ከእኔ እንዲርቁ አደረግህ፤
በፊታቸውም አጸያፊ አደረግኸኝ፤
ዙሪያዬ ታጥሮአል፤ ማምለጫም የለኝም።
9ሐዘኔ ከመብዛቱ የተነሣ ዐይኖቼ ደከሙ፤
እግዚአብሔር ሆይ! በየቀኑ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤
እጆቼንም ለጸሎት ወደ አንተ እዘረጋለሁ።
10ለሙታን ተአምራትን ታደርጋለህን?
እነርሱስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን?
11ዘለዓለማዊ ፍቅርህ በመቃብር፥
ታማኝነትህ በጥፋት ቦታ ይነገራልን?
12ተአምራትህ በጨለማ ስፍራ ይታወቃሉን?
ታዳጊነትህስ በተረሱ ሰዎች አገር ይታያልን?
13እግዚአብሔር ሆይ!
እንድትረዳኝ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤
በየማለዳውም ወደ አንተ እጸልያለሁ።
14እግዚአብሔር ሆይ! ለምን ትጥለኛለህ?
ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?
15ከልጅነቴ ጀምሮ ጭንቀት ደርሶብኝ
እስከ ሞት ተቃርቤአለሁ፤
ከማስደንገጥህ የተነሣ ተስፋ ቈርጬአለሁ።
16ብርቱ ቊጣህ አደቀቀኝ፤
አስፈሪው ቅጣትህ ያጠፋኛል።
17እነርሱ ቀኑን ሙሉ እንደ ጐርፍ ከበቡኝ፤
ፈጽመውም አሰጠሙኝ።
18የቅርብ ወዳጆቼንና ጓደኞቼን ከእኔ አርቀህ
ጨለማ ብቻ ከእኔ ጋር እንዲቀር አደረግህ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ