መጽሐፈ መዝሙር 5
5
የመማጠኛ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! ቃሌን አድምጥ፤
መቃተቴንም ስማ።
2ንጉሤና አምላኬ ሆይ!
ወደ አንተ ስለምጸልይ
ለእርዳታ የምጮኸውን ጩኸት አድምጥ።
3እግዚአብሔር ሆይ! ልመናዬን ወደ አንተ አቅርቤ መልስህን ስጠብቅ
በየማለዳው ጸሎቴን ስማ።
4አንተ በኃጢአት የምትደሰት አምላክ አይደለህም፤
ክፉዎችም ከአንተ ጋር አይኖሩም።
5ትዕቢተኞች በፊትህ አይቆሙም፤
ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ትጠላለህ።
6ሐሰት የሚናገሩትን ሁሉ ታጠፋለህ፤
ነፍሰ ገዳዮችንና አታላዮችን ትጸየፋለህ።
7እኔ ግን በታላቅ ምሕረትህ ወደ ቤትህ እገባለሁ፤
ወደ ቤተ መቅደስህ በአክብሮት እሰግዳለሁ።
8እግዚአብሔር ሆይ! የሚጠባበቁኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው!
ስለዚህ ፈቃድህን እንዳደርግ ምራኝ፤
መንገድህንም በፊቴ አቅናልኝ።
9ጠላቶቼ የሚናገሩት ሁሉ ከእውነት የራቀ ስለ ሆነ፥
ከአፋቸው እውነት አይገኝም፤ ሐሳባቸውም በተንኰል የተሞላ ነው፤
ጒሮሮአቸውም እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤
በምላሳቸውም ሰውን ይሸነግላሉ። #ሮም 3፥13።
10አምላክ ሆይ! ፍረድባቸው፤
የራሳቸው ሤራ መውደቂያቸው ይሁን፤
በአንተ ላይ ስለ ዐመፁ ስለ ብዙ በደላቸው አስወግዳቸው፤
11በአንተ ከለላ ሥር ያሉ ሁሉ ይደሰቱ፤
ለዘለዓለምም እልል ይበሉ
የአንተን ስም የሚወዱትን ሁሉ በደስታም እንዲፈነድቁ ከልላቸው።
12እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ጻድቃንን ትባርካለህ፤
በቸርነትህም እንደ ጋሻ መከላከያ ትሆንላቸዋለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997