የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 25

25
የእግዚአብሔርን መሪነትና ጠባቂነት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! የልቤን ሐሳብ ወደ አንተ አቀርባለሁ።
2አምላኬ ሆይ! በአንተ እታመናለሁ፤
ጠላቶቼ ድል እንዲቀዳጁ አድርገህ አታሳፍረኝ።
3በአንተ የሚታመኑት ኀፍረት አይደርስባቸውም፤
ኀፍረት የሚደርስባቸው፥
በአንተ ላይ ለማመፅ የሚጣደፉት ናቸው።
4አምላክ ሆይ! ዱካህን እንዳውቅ አድርገኝ፤
መንገድህንም አስተምረኝ።
5አንተ የምታድነኝ አምላኬ ነህና
እውነትህን ተከትዬ እንድኖር አስተምረኝ፤
እኔ ዘወትር የምታመነው በአንተ ነው።
6እግዚአብሔር ሆይ!
ከጥንት ጀምሮ የምታሳየውን
ምሕረትና ዘለዓለማዊ ፍቅር አስብ።
7አምላክ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ
አስበኝ እንጂ የወጣትነት ኃጢአቴን
ወይም በደሌን አታስብብኝ!
8እግዚአብሔር ደግና ቀጥተኛ ስለ ሆነ፥
ሊከተሉት የሚገባቸውን መንገድ
ለኃጢአተኞች ያስተምራል።
9ትሑቶችንም በትክክለኛው መንገድ ይመራቸዋል፤
መንገዱንም ያስተምራቸዋል።
10የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትእዛዞች ለሚጠብቁ ሰዎች
የእግዚአብሔር መንገዶች ሁሉ ፍቅርና ታማኝነት ናቸው።
11እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ስምህ ክብር
እጅግ የበዛውን ኃጢአቴን ይቅር በልልኝ።
12እግዚአብሔርን የሚፈሩ እነማን ናቸው?
እነርሱ መከተል የሚገባቸውን አካሄድ እንዲመርጡ እርሱ ያስተምራቸዋል።
13ዘወትር በብልጽግና ይኖራሉ፤
ልጆቻቸውም ምድርን ይወርሳሉ።
14እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ ወዳጃቸው ነው፤
ለእነርሱ የገባውንም ቃል ኪዳን ያጸናል።
15ከወጥመዶች ሁሉ ስለሚያድነኝ
ሁልጊዜ ወደ እርሱ እመለከታለሁ።
16እኔ ብቸኛና ችግረኛ ስለ ሆንኩ
አምላክ ሆይ! ወደ እኔ ተመለስ፤
በጎነትንም አድርግልኝ።
17ከደረሰብኝ ችግር ሁሉ
እንድላቀቅ አድርገኝ፤
ከጭንቀቴም ሁሉ አድነኝ።
18ችግሬንና ሥቃዬን ተመልከት፤
ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በልልኝ።
19ጠላቶቼ ምን ያኽል እንደ በዙ እይ፤
ምን ያኽል እንደ ጠሉኝም ተመልከት።
20ጠብቀኝ፤ አድነኝም፤
አንተን መጠጊያ ስላደረግሁ
ኀፍረት እንዲደርስብኝ አታድርግ።
21አምላክ ሆይ! አንተን ተስፋ አደርጋለሁ፤
ቅንነትና ቀጥተኛነት እንዲጠብቁኝ አድርግ።
22አምላክ ሆይ! እስራኤልን
ከመከራው ሁሉ አድን!

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ