መጽሐፈ መዝሙር 106:24-48

መጽሐፈ መዝሙር 106:24-48 አማ05

በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስላልተማመኑ መልካሚቷን ምድር ናቁ። በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው አጒረመረሙ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አንሰማም አሉ። ስለዚህ እጁን አንሥቶ በመማል በበረሓ የሚያጠፋቸው መሆኑን ነገራቸው፤ ዘሮቻቸውን ሁሉ በአሕዛብ መካከል እንደሚጥላቸውና በመላው ዓለም እንደሚበታትናቸው ገለጠላቸው። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ በፔዖር የነበረውን ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ጣዖት አመለኩ፤ ሕይወት ለሌላቸው አማልክት የቀረበውንም የመሥዋዕት ሥጋ በሉ። በክፉ ሥራቸው እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በዚህ ምክንያት መቅሠፍት በመካከላቸው ተነሣ። ነገር ግን ፊንሐስ ተነሥቶ በደል የፈጸሙትን በቀጣቸው ጊዜ መቅሠፍቱ ተወገደ። ይህም አድራጎቱ ወደ ፊት ለሚከተለው ትውልድ ለዘለዓለም እንደ መልካም ሥራ ሆኖ ተቈጠረለት። በመሪባ ምንጮች አጠገብ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በእነርሱም ምክንያት ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ። እጅግ አስመርረውት ስለ ነበር ሙሴ ራሱን ባለመቈጣጠር ተናገረ። እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት አሕዛብን አላጠፉም፤ እንዲያውም ከእነርሱ ጋር ተደባልቀው የኑሮ ሥርዓታቸውን ተከተሉ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች የአሕዛብን ጣዖቶች አመለኩ፤ ይህም ለጥፋታቸው ምክንያት ሆነ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንትና በከነዓን አገር ለሚገኙ ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነርሱ ለከነዓን ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በመግደል ንጹሕ ደም አፍስሰዋል፤ ምድሪቱም በደም ረከሰች። እነርሱ በሥራቸው ረከሱ፤ በክፉ ሥራቸውም እግዚአብሔርን ካዱ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተቈጣ፤ እጅግም ተጸየፋቸው። ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጠላቶቻቸውም ገዥዎቻቸው ሆኑ። በጠላቶቻቸው ተጨቊነው ፈጽሞ የእነርሱ ተገዢዎች ሆኑ። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ታድጎአቸዋል፤ እነርሱ ግን በእርሱ ላይ ማመፅን መረጡ፤ ስለዚህ ኃጢአታቸው ለውድቀታቸው ምክንያት ሆነ። ይህም ሁሉ ሆኖ እንደገና ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበት ጊዜ ይሰማቸው ነበር፤ ሥቃያቸውንም ይመለከት ነበር። እነርሱን ለማዳን ቃል ኪዳኑን ያስታውስ ነበር፤ ስለ ታላቅ ፍቅሩም ምሕረት ያደርግላቸው ነበር። የሚጨቊኑአቸው ሁሉ እንዲራሩላቸው አደረገ። እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አድነን! ከመንግሥታት መካከል መልሰህ ወደ አገራችን አግባን፤ በዚያን ጊዜ እናመሰግንሃለን፤ ቅዱስ ስምህንም እናከብራለን። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! ሕዝቡ ሁሉ አሜን አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመስግኑ።