የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 106:1-15

መጽሐፈ መዝሙር 106:1-15 አማ05

እግዚአብሔርን አመስግኑ! ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ! እርሱ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች ማን ቈጥሮ ሊደርስባቸው ይችላል? የሚገባውንስ ያኽል ሊያመሰግነው የሚችል ማን ነው? ፍትሕን የሚከተሉና ዘወትር ትክክለኛ የሆነውን ነገር የሚያደርጉ፥ እንዴት የተባረኩ ናቸው? እግዚአብሔር ሆይ! ሕዝብህን በምትረዳበት ጊዜ እኔንም አስታውሰኝ፤ እነርሱን በምታድንበት ጊዜ እኔንም አስበኝ። በአንተ ከሚመኩት ወገኖችህ እንደ አንዱ ሆኜ፥ ሕዝቦችህ ሲበለጽጉ እንዳይና የወገኖችህንም ደስታ እንድካፈል አድርገኝ። እንደ ቀድሞ አባቶቻችን ኃጢአት ሠርተናል፤ ተሳስተናል፤ በደለኞችም ሆነናል። የቀድሞ አባቶቻችን በግብጽ ምድር እርሱ ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ አላስተዋሉም፤ ብዙዎቹን የቸርነት ሥራዎቹን አላስታወሱም፤ በቀይ ባሕር አጠገብ ዐመፁ። ሆኖም ኀያል ሥልጣኑን ለማሳወቅ ስለ ክብሩ አዳናቸው። ቀይ ባሕርን በገሠጸው ጊዜ ደረቀ፤ ጥልቁን ውሃ እንደ በረሓ አድርጎ ሕዝቦቹን እየመራ አሻገራቸው። ከሚጠሉአቸውም ሰዎች እጅ አዳናቸው፤ ከጠላቶቻቸውም እጅ ታደጋቸው። ጠላቶቻቸውን ግን ውሃው አሰጠማቸው፤ ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት የቀረ አልነበረም። ከዚህ በኋላ በተስፋ ቃሉ አመኑ፤ የምስጋናም መዝሙር ዘመሩለት። ይሁን እንጂ ያደረገላቸውን ድንቅ ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ረሱ፤ የእርሱንም ምክር ሳይጠብቁ የራሳቸውን ፈቃድ አደረጉ። በበረሓ ሳሉ ብዙ ነገር ተመኙ፤ እግዚአብሔርንም ተፈታተኑት። እርሱ የለመኑትን ሁሉ ሰጣቸው፤ ነገር ግን የሚያመነምን በሽታ አመጣባቸው።