መጽሐፈ ምሳሌ 9
9
ብልኅነትና ሞኝነት
1ጥበብ ቤትዋን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶዎችንም ለቤትዋ አቆመች። 2ላዘጋጀችውም ግብዣ ፍሪዳ ዐረደች፤ የጣፈጠ የወይን ጠጅም ጠመቀች፤ ገበታም ዘርግታ ማእድ ሠራች። 3ገረዶችዋም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ቆመው፥ 4“ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ሁሉ ወደዚህ ኑ!” እያሉ እንዲጣሩ አደረገች፤ ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች። 5“ና ያዘጋጀሁትን ምግብ ብላ! የጠመቅኩትንም የወይን ጠጅ ጠጣ! 6ዕውቀት ከጐደላቸው ሰዎች ተለይ! በሕይወትም ትኖራለህ፤ በማስተዋልም መንገድ ወደፊት ተራመድ።”
7ትዕቢተኛን ሰው ብታርመው ስድብን ታተርፋለህ፤ ክፉውን ሰው ብትገሥጸው ጒዳት ይደርስብሃል። 8ትዕቢተኛን ሰው ብታርመው ይጠላሃል፤ ጠቢብን ሰው ብታርመው ግን ይወድሃል። 9ጠቢብን አስተምረው፥ በይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ ደግን ሰው አስተምረው፤ ዕውቀትን ይጨምራል።
10እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። #ኢዮብ 28፥28፤ መዝ. 111፥10፤ ምሳ. 1፥7። 11በእኔ አማካይነት ዕድሜህ ይረዝማል፤ ለሕይወትህም ዓመቶች ይጨመራሉ። 12ጥበብ ቢኖርህ ጥቅሙ ለራስህ ነው፤ ፌዘኛ ብትሆን የምትጐዳው ራስህን ነው።
13ዕውቀትን ማጣት፥ እንደ ለፍላፊ፥ ምንም ነገር እንደማታውቅ ደንቈሮና ኀፍረተቢስ ሴት መሆን ነው። 14እርስዋ በቤትዋ በር ላይ ወይም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ትቀመጣለች፤ 15ሥራቸውን በቅንነት እየሠሩ በመንገድ የሚያልፉትን ሁሉ እንዲህ እያለች ትጣራለች፦ 16“እናንተ ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ወደ እኔ ኑ!” ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች፦ 17“ሰርቀው የሚጠጡት ውሃ ይጣፍጣል፤ ተሸሽገው የሚበሉትም እንጀራ ያስደስታል።” 18እርሱም ወደ ቤትዋ የሚሄዱ ሁሉ እንደሚሞቱና እስከ አሁንም ወደ ቤትዋ የገቡ ወደ ሙታን ዓለም ተሽቈልቊለው እንደወረዱ አያውቅም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997